በትምህርት ቤቶች በሃሳብ የመከራከር ባህል እንዲዳብር መስራት ይገባል ተባለ

65
ነሀሴ16/2011''በሃሳብ የመከራከር ባህል አለማደጉና ቀደም ሲል የነበረውም እየቀረ በመምጣቱ የሐሳብ ልዩነትን መሸከም የማይችል ትውልድ እንዳበራከት ማድረጉ ተገልጿል። በጥንት ኢትጵያ  በስፋት ይስተዋል የነበረው የሃሳብ ክርክር እየቀረ በመምጣቱ የሐሳብ ልዩነትን ሊሸከም የማይችል ትውልድ እየተበራከተ መጥቷል ተብሏል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ አስተባባሪነት በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መካከል በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው ''ብሄራዊ የክርክር ውድድር'' ተጠናቋል። በውድድሩም የጅማ ዪኒቨርስቲ ተማሪ የሆነችው ንጹህ ደጀኔ በክርክሩ አሸናፊ ሆናለች። በሃሳብ ክርክር መሸናነፍ በሃሳብ የበላይንት ወደ ፊት መራመድ ያስችላል የምትለው ተማሪ ንጹህ ይህ ልምድ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ትላለች። በተለያዩ ሐሳቦች የክርክር ባህልን ማዳበርና ማሳደግ አገራዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ገልጻለች። በተለይም ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ ተማሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመከራከር የሃሳብ የበላይነትን በቅጡ እንዲረዱ ማድርግ ይገባልም ብላለች። ይህ ከሆነ የሃሳብ ልዩነትን የሚቀበልና አለመባባቶችን በመነጋገር ሊፈታ የሚችል ትውልድ ማፍራት እንደሚቻል ታምናለች። በክርክር ውድድሩ ሁለተኛ በመሆን ያጠናቀቀችው የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪ አርሴማ ስዩም በበኩሏ አለመግባባቶች በውይይትና በምክንያታዊነት መፍታት ለአገር ዲሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ተናገራለች። ''ግጭቶች እየተከሰቱ ያሉት ባለመግባባት ነው የምትለው'' ተማሪዋ በመነጋገር ከሆነ ግን የማይፈታ ጉዳይ የለም ብላለች። ኩነቱን ያዘጋጀው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ ሲሆን በአገሪቷ ከ14 ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ 28 ተማሪዎች ተሳትፈዋል። ለዚሁ የክርክር ሂደትም ለአንድ ዓመት ያክል ስልጠና ሲሰጥ እንደቆየ ተገልጿል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክር ራይነር እንደገለጹት አገራዊ የክርክር ውድድሩ አላማ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ያላቸውን ክህሎት፣ ተግባቦትንና እውቀት የሚያጎለብቱበት አማራጭ ነው። በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተማሪዎች እንዲከራከሩ በማድርግ ተግባቦትን ማዳበር የሚያስችል ነውም ብለዋል። ክርክሩ የመናገር ነጻነትንና ልዩነቶችን ማስተናግድ የሚችል ማህበረሰብ መፍጠር ዋነኛ አላማው መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ ይህም በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታን ያግዛል ብለዋል። የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሚኒስትር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንደዚህ አይነት የክርክርና የውይይት ልምዶች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲስፋፉ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። ይህ ልምድ ለአገሪቷ የዲሞክራሲ፣ የሰላምና የአብሮነት እሴት መጎልበት ጉልህ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል። በመጨረሻም የክርክር ክለቡ እንዲቋቋምና እንዲዘጋጅ ላደረገው የአሜሪካ መንግስት ምስጋና አቅርበዋል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም