አየርላንድ ለኢትዮጵያ የልማት ስራዎች የምታደርገውን ድጋፍ ትቀጥላለች-አምባሳደር ሳንጃ ሃይላንድ

85
ነሀሴ 15/2011አየርላንድ ለኢትዮጵያ የልማት ስራዎች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተሰናባቿ በኢትዮጵያ የአየርላንድ አምባሳደር ሳንጃ ሃይላንድ ተናገሩ። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የስራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የአየርላንድ አምባሳደር ሳንጃ ሃይላድን በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ተቀብለው አስናብተዋል። አምባሳደሯ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና አየርላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩ 25 ዓመታትን አስቆጥረዋል። በእነዚህ ዓመታት አገራቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመቀናጀት በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ ድጋፍ ማድረጓን አብራርተዋል። አየርላንድ ቀጣዩን የኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት እና በፓርላማ ውስጥ እየተከናወነ ያለውን ለውጥ መደገፍ የሚያስችላት ስምምነት ከጥቂት ቀናቶች በፊት ከኢትዮጵያ ጋር መፈራረሟን ገልጸዋል። በቆይታቸው የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶችን የስራ ምህዳር የሚያሰፋ አዲስ ህግ በኢትዮጵያ ስራ ላይ እንዲውል አየርላንድ ያደረገችው ድጋፍ ልዩ ደስታ እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል። አየርላንድ "በአይሪሽ ኤድ" አማካኝነት በተለያዩ አገራት እየተገበረች ካለችው የልማት ፕሮግራም ውስጥ ትልቁን በኢትዮጵያ እንደምታከናውን አምባሳደር ሃይላንድ አውስተዋል። ድጋፉ በዋናነት እንደ ግብርና፣ ጤና እንዲሁም ሰላምና ደህንነትን በመሳሰሉ ዘርፎች ላይ እንደሚያተኩር ጠቁመው፤ ይህ ድጋፍ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አብርሃም ግርማይ አምባሳደሯ በስራ ዘመናቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት እንዲጠናከር መስራታቸውን አስታውሰዋል። በቀጣይ ግንኙነቱ ይበልጥ እንዲጎለብት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ለፕሬዝዳንቷ መግለጻቸውንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያና አየርላንድ ሁለትዮሽ ግንኙነት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይበልጥ እየተጠናከረ የመጣ  ሲሆን፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ገዥ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም