በህገ ወጥ መንገድ ሆሳዕና ከተማ የገባ 8 ሺህ 700 ሌትር ቤንዚል ተያዘ

90
ሆሳዕና ኢዜአ ነሐሴ 15 / 2011 - በህገ ወጥ መንገድ ወደሆሳዕና ከተማ የገባ 8 ሺህ 700 ሌትር ቤንዚል መያዙን የከተማዉ ፖሊስ አስታወቀ። የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዣዥ ተወካይ ኢንስፔክተር ምስጋኑ ልውሞሎ ለኢዜአ እንደገለጹት ቤንዚሉ ትናንት ሊያዝ የቻለው በሰሌዳ ቁጥር 3- 20173 አ.አ በሆነ ኤፍ ኤስ አር የጭነት መኪና ከሌላ አካባቢ ተጭኖ ወደ ከተማው ከገባ በኋላ በግለሰብ ቤት እየወረደ ባለበት ወቅት ነው። ከህብረተሰቡ ለፖሊስ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በተደረገ ክትትል 8 ሺህ 700 ሌትር ቤንዚል እጅ ከፍንጅ መያዙን አመልክተዋል፡፡ የመኪናው ሾፌር ለጊዜው መሰወሩን የተናገሩት ኢንስፔክተሩ የቤንዚሉ ባለቤት ተይዞ ፖሊስ የምርመራ ስራውን እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ ያለህብረተሰቡ ተሳትፎ ወንጀልን በመከላከል ውጤታማ እንደማይሆን የተናገሩት ኢንስፔክተር ምስጋኑ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በመሆን ወንጀልን ለመከላከል የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲያጠናክር አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም