የደብረ ታቦር በዓልን ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ---ዶክተር ሒሩት ካሳው

116
ነሀሴ 15/2011 የደብረ ታቦር በዓልን ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴት ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ካሳው አስገነዘቡ ። “ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር” በሚል መሪ ቃል የቡሄ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ዶክተር ሒሩት ካሳው በወቅቱ እንደገለጹት እንደ ቡሄ በዓል ያሉ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎችን በዘመናዊ መንገድ ማጥናት፣ ማበልጸግና ማስተዋወቅ ይገባል። የደብረ ታቦር በዓል ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ከተከበረ የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን በመሳብ ማህበራዊና ኢኮኖሚኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሚሆን አመላክተዋል ። የበዓሉ ማድመቂያ የሆነውን ሆያ ሆዬ የህጻናትና የወጣቶች ባህላዊ ጨዋታን ለትውልድ ለማስተላለፍ የተጀመረው መልካም ጅምር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዘበዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በህብረተሰቡ ውስጥ ለዘመናት የቆዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶችን በማልማት ለህዝቦች አንድነት፣ መተሳሰብና መተሳሰር ለማዋል እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል ። የደቡብ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መላከ ጸሐይ ጸዳሉ የደብረ ታቦር ኢየሱስ ተራራ የተሰየመው በእስራኤል ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮቱን በገለጸበት ተራራ ምሳሌ መሆኑን ተናግረዋል ። በዓሉ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ትስስር ባለው በደብረ ተቦር ኢየሱስ ተራራ በህጻናትና ወጣቶች ሆያ ሆዬና አሸንድዬ ባህላዊ ክዋኔዎችና ሃይማኖታዊ ይዘት ባለው በተክሌ ዝማሜ መከበሩንም ገልጸዋል ። "በዓሉ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጾታና በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ልዩነት ሳይፈጠር በአንድነት የሚከበር መሆኑ ለዘመናት የዘለቀውን ህዝባዊ ትስስር ያሳያል" ብለዋል። ወጣት ገብረማርያም ጳውሎስ በበኩሉ ሆያ ሆዬ ከትውልድ ወደ ትውልት ሲተላለፍ የመጣ ባህላዊ ጨዋታ መሆኑን ነው የገለጸው። "ለበዓሉ የሚሆኑ ግጥሞችና ስነ ቃሎችን በመድረስና ቁሳቁስ በማዘጋጀት በዓሉን ማክበሩን ተናግሯል" ብሏል ። "የመፈቃቀር፣ የመዋደድ፣ የመረዳዳትና አብሮ የመብላት እሴትን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ በዓሉ መልካም አጋጣሚ እየፈጠረልን በመምጣቱ እኔና ጓደኞቼ ደስተኞች ነን " ሲል ጨምሮ ገልጻል ። "ወጣት ማስተዋል ወንዴ በበኩሏ የአሸንድዬ ጨዋታ ከሆያ ሆዬ ጋር አብሮ የሚከወን የሴትና ወንድ ህጻናትና ወጣቶች የነጻነትና እኩልነት ማሳያ ነው" ብላለች። በዓሉን በአንድ ቦታ መከበሩ ለትውልድ እንዲተላለፍ አስተዋጾ የጎላ መሆኑንም ተናግራለች ። በዓሉን በማስመልከት በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የፓናል ውይይት ተካሂዷል። በዓሉ ከትናንት በስቲያ በደበረ ታቦር ከተማ አስተዳደር፣ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲና በዞኑ ሃገረ ስብከ ትብብር የተከበረ ሲሆን የክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ኃላፊዎች፣ ምሁራንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም