ለወላይታ ድቻ ቡድን ከ300 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ

56
ሶዶ (ኢዜአ) ነሀሴ 15 ቀን 2011- የዘንድሮ ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ለሆነው የወላይታ ድቻ ቡድን የ300 ሺህ ብር ድጋፍም ተደርጓል። ትናንት ማምሻውን በሶዶ ከተማ ደማቅ አቀባበል ተደረጎለታል፡፡ ለቡድኑ ደጋፊዎቹና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ደማቅ አቀባበል የተደረገ ሲሆን፣ የወላይታ ዞን አስተዳደርም 300 ሺህ ብር የማበረታቻ ድጋፍ አድርጓል። የወላይታ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የወላይታ ድቻ ስፖርት ክለብ ፕሬዚዳንት አቶ ፍሬው ሞገስ የቡድኑ ስኬት በአካባቢው ያለውን የስፖርት አቅም ለመጠቀም፣ ዋናውን ቡድን ለመመገብና ታዳጊዎችን ለማፍራት የተነደፈው ስትራቴጂ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል። የዞኑ አስተዳደር ለቡድኑ ማበረታቻ እንዲሆን የ300 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል። በቀጣይም ህብረተሰቡን በማስተባበር የቡድኑን ደረጃ በማሳደግ የተሻለ ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ የዞኑ አስተዳደር በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል። የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ሆሲሶ ቡድኑ ፈታኝ የሆነ የውድድር ጊዜ ቢያሳልፍም ዋንጫ ለማንሳት በተያዘ ዕቅድ መሠረት ስኬታማ መሆናቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። ክለቡ በሚሳተፍባቸው ሁሉም የውድድር ዘርፎች ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የገለጹት አቶ አሰፋ ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት ባለፈ ለሀገር የድርሻቸውን አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ስፖርተኞችን ለማፍራት ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል ። ከ20 ዓመት በታች የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ግዛቸው ጌታቸው ውድድሩ ከወትሮ በተለየ መልኩ ከፍተኛ ፉክክር የነበረበት እንደነበር አስታውሰዋል። የተደረገላቸው አቀባበልና ድጋፍ ለበለጠ ውጤት የሚያነሳሳቸው መሆኑን ገልጸዋል። የግብ አጋጣሚ ፈጥረው መጠቀማቸው፣ የአካል ብቃትና ስነምግባር ተላብሰው መጫወታቸው እንዲሁም ያገኙትን ስልጠና በአግባቡ መተግበራቸው ለስኬት እንዳበቃቸው የገለጸው ደግሞ የቡድኑ አምበል ምስክር መለሰ ነው። የተደረገላቸው ድጋፍና ደማቅ አቀባበል በቀጣይ ከዚህ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሞራል ስንቅ እንደሆናቸው አመልክቷል ። የዘንድሮ ከ20 ዓመት በታች የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ማጠቃለያ ውድድር በስድስት ቡድኖች መካከል በአዳማ ከተማ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል። ወላይታ ድቻ እግር ኳስ ቡድን ዋንጫውን ሲያነሳ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም