ሱዳን 11 አባላት ያሉትን ሉዓላዊ የሽግግር ሸንጎ በይፋ መሰረተች

52

ኢዜአ፤ ነሐሴ 15/2011 የሱዳን ወታደራዊ መሪዎች እና የነጻነትና የለውጥ ኃይሎች 11 አባላት ያሉትን ጥምር ሉዓላዊ የሽግግር ሸንጎ ይፋ አድርገዋል።

የሽግግር ሸንጎው ከወታደሩ አምስት ከነጻነትና የለውጥ ኃይሎች አምስት እንዲሁም የኮፕቲክ ክርስትና አማኝ የሆኑ አንድ ገለልተኛ አባል ያካተተ ሲሆን ሱዳንን ለሚቀጥሉት 3 ዓመታት ይመራል።

የቀድሞ የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሺርን ከስልጣን አውርዶ ሀገሪቱን ሲመራ የቆየው ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ቃል አቀባይ በወታደሩ በኩል ለሉዓላዊ ምክር ቤቱ የተሰየሙትን ይፋ አድርገዋል።

በዚህ መሰረትም ሉዓላዊ ምክር ቤቱን በበላይነት ለሚቀጥሉት 21 ወራት የሚመሩትን ጀኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃንን ጨምሮ፣ ጀኔራል ሞሃመድ ሀምዳን ደገሎ፣ያሰር አታ፣ ኢብራሂም ጋበር እና ሻምስ አል ዲን ካባሺ ወታደሩን ወክለዋል።

በነጻነትና የለውጥ ኃይሎች በኩል ለሉዓላዊ ምክር ቤቱ የተሰየሙት አምስት ሲቪል አባላት ደግሞ ሀሰን ሞሃመድ ኢድሪስ፣ አል ሲዲቅ ታወር ካፊ፣ አይሻ ሳ ሰኢድ፣ ሞሃመድ ኡስማን ሀሰን አልታይሺ እና ራጃ ኒኮላ ኢሳ አብዱ ማሴህ ናቸው።

ከሲቪል አባላቱ መካከል ሴት እና ጋዜጠኛ ይገኙበታል ተብሏል።

በሌላ በኩል 11ኛ የምክር ቤቱ አባል ሆነው በገላጋይነት ታምኖባቸው በሁለቱም ወገን የተመረጡት አንድ የኮፕቲክ ክርስቲያን ናቸው።

የሉዓላዊ ምክር ቤቱ አባላት እና አዲሱ የሽግግር ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር በዛሬው ዕለት ቃለ መሃላ ፈጽመው ስራቸውን እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።

የሱዳን የነጻነትና የለውጥ ኃይሎች ነን የሚሉት የተቃውሞ መሪዎች ባሳለፍነው ሳምንት አንጋፋውን የኢኮኖሚ ባለሙያ አብደላ ሃምዶክን በእጩ ጠቅላይ ሚኒስትርነት አቅርበዋል።

የወታደሩ መሪዎች ተቃዋሚዎች 300 አባላት ያሉት የሽግግር ጊዜ የህግ አውጭ ምክር ቤት እና አስተዳደራዊ ካቢኔ ለማቋቋም ተስማምተዋል።

የአል በሺርን ከስልጣን መውረድ ተከትሎ በሱዳን ለውጥና ዴሞክራሲ እስካልመጣ ድረስ ተቃውሟችንን አናቆምም በሚሉ ሱዳናውያን ላይ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በርካታ ሰዎች ሞተዋል።

ከታህሳስ ወር 2018 ጀምሮ ለተቃውሞ ወደ አደባባይ በወጡ ሰዎች ላይ በተወሰደ እርምጃ 250 ሰዎች እንደተገደሉም መረጃዎች ያሳያሉ።

የአፍሪካ ህብረት እና ኢትዮጵያ ባደረጉት ወታደሩን እና ተቃዋሚዎችን የማደራደር ጥረት ባሳለፍነው ቅዳሜ ሱዳናውያኑ የመጨረሻውን ስምምነታቸውን ተፈራርመዋል ሲል የዘገበው አል ጄዚራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም