በወራቤ ከተማ የአመራሮች ግምገማ ተጀመረ

59
ሆሳእና ኢዜአ ነሐሴ 14/2011፡- “ህብረ ብሄራዊ አንድነታችን ለጋራ እድገታችን እና ለተደማጭነታችን መሰረት ነው” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የአመራሮች የግምገማ መድረክ ዛሬ በወራቤ ከተማ ተጀመረ። በዚህ ወቅት የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል  ወይዘሮ ማርታ ለውጂ እንዳሉት ለሶስት ቀናት በሚቆየው  መድረክ በሀገራዊና ክልላዊ የፖለቲካና ሰላም ዙሪያ  የስልጤ ዞን አመራሮች የነበራቸው ሚና ይገመገማል። በክልሉ በሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎች ዙሪያ በምሁራን የተካሄደውን የጥናት ሰነድ ከክልሉ ህዝብ ተጠቃሚነት አንጻር አመራሩ በጥልቅት ይወያያል፡፡ በዚህ መነሻነት  የዞኑ አመራር የክልሉ መገለጭ የነበረውን አብሮነትንና  አንድነት ቀጣይነት እንዲኖረው ወደ ህዝቡ በመግባት ጠንክሮ እንዲሰራ በማድረግ ረገድ እንደሚመክርም ወይዘሮ ማርታ አስረድተዋል። "በወቅቱ የተፈጠረውን የአመራር ስርዓት ብልሹ መሆን በፖለቲካው ላይ የፈጠረው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ለሰው ህይወት ማለፍና ንብረት መውደም ምክንያት ነው" ያሉት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አማካሪ አቶ ማሙሽ ሁሴን ናቸው፡፡ አመራሩ ከድርጅቱ የተሰጠውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው  ብሄርተኝነትን በማጠናከር የሰላምና የአብሮነት ተምሳሌት የነበረውን ክልል ለማፍረስ ቀውስ በመፍጠር ተሳታፊ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡ የዞኑ ህዝብ ያለ ቦታ ገደብ ተንቀሳቅሶ በንግድ ራሱንና ሀገሪቱን ሊደግፍ በሚችል ደረጃ ተጠቃሚ በመሆኑ ይህንን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል አመራር መስራት እንዳለበት ተመልክቷል፡፡ በመድረኩ አመራሩ የሚስተዋልበትን ችግር በመፍታት  በድርጅታዊ መርህ በመጓዝ አብሮነትን የሚያጠናክር አቅጣጫ እንደሚያቀመጥ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም