የክረምቱ ወቅት ዝናብ ተጠናክሮ ይቀጥላል – – ብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ

201

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 14/2011 በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል እየጣለ ያለው የክረምቱ ዝናብ በቀሪዎቹ ጊዜያትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ያለፉት ወራትንና ቀሪውን የክረምት ወቅት አስመልክቶ ዛሬ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት በተያዘው የነሃሴ ወር ቀሪ ቀናትና በመስከረም ወር 2012 ዓም የክረምቱ ዝናብ በብዙዎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ተስፋፍቶ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህም እየተካሄደ ላለው የግብርና ልማት ስራ በተለይም ለውሃ ሴክተር ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ነው አቶ ፈጠነ የተናገሩት።

አክለውም አልፎ አልፎ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ በአንዳንድ ቦታዎች የሚጠበቅ መሆኑንም አስረድተዋል።

ያለፉት የክረምት ወራት የዝናብ ስርጭት በብዙ ቦታዎች ቀድሞ የመግባት አዝማሚያ ያሳየ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ ብዙዎቹ የአገሪቱ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ አግኝተዋል ብለዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎችም ከመደበኛ በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ መመዝገቡን አመልክተዋል።

በዚህም ሳቢያ በአንዳንድ ስፍራዎች የተከሰተው ጎርፍ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ አደጋ ማስከተሉን ገልፀዋል።

በአባይ ተፋሰስ ፎገራ፣ የርብ ግድብ፣ የአዋሽ ተፋሰስ፣ የባሮ ተፋሰሶችና አካባቢው ሙሉ ለሙሉ ለጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች መሆናቸውም ተገልጿል።