አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የነገሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

51
ነገሌ ሰኔ 6/2010 በመቻቻልና በመደማመጥ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የነገሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ነዋሪዎቹ በሀገራዊና በአካባቢያው ወቅታዊ የሰላምና ልማት ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ በከተማው ሁለገብ የእግር ኳስ ሜዳ ተወያይተዋል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የከተማው ቀበሌ አንድ  ነዋሪ አቶ ደጀኔ ታደሰ በሰጡት አስተያየት "የሰላምና የልማት ጥያቄ በህጋዊ መንገድ ቀርቦ በመደማመጥና በመወያየት ሊፈታ ይገባል "ብለዋል፡፡ የወሰን  ጉዳይ ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር ከውይይት በቀር እርስ በርስ በመካሰስና በመወነጃጀል ሊፈታ እንደማይችል በተግባር እየታየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጠሩ ስህተቶች እንዳይደገሙ ችግሮች በመቻቻልና በመደማመጥ እንዲፈቱ የሚደረጉ ጥረቶችን በመደገፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ ሌላው  የውይይቱ ተካፋይ ወጣት መላኩ ፈለቀ በበኩሉ " ወጣቶች ሰርተን የምንለወጥበትን ጊዜ በረብሻና ብጥብጥ ማባከን የለብንም " ብሏል፡፡ አባቶች ካቆዩት የመቻቻል ፣ የመረዳዳትና የመደማመጥ ባህል ትምህርት በመውሰድ ከስሜት ነጻ ሆኖ ለሰላምና ለልማት መስራት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ ባለፉት ዓመታት ስሜታዊ በሆነ አካሄድ ከጠፋ የሰው ህይወትና ንብረት ትምህርት መውሰድ እንደሚገባ ያመለከተው ደግሞ  ወጣት ደንደና ሙሉጌታ ነው፡፡ አሁን የተገኘውን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል ወጣቱ ፣አመራሩ ፣ አባቶችና ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል  የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቅሶ መንግስት የወጣቶችን ስራ አጥነት ችግር ለመፍታት የጀመረውን ተግባር እንዲያጠናክርም ጠይቋል፡፡ ውይይቱን የመሩት የነገሌ ከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደበሊ ለሚ መንግስት ከህዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ምላሽ ለመስጠት  በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "ካሁን በፊት በህዝቡ የተነሱ  ጥያቄዎች በዘላቂነት ምላሽ ለመስጠት የአጭር ፣የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድ ወጥቶ በቅደም ተከተል እየተተገበረ ነው "ብለዋል፡፡ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ህብረተሰቡም በመደገፍ እገዛውን እንዲያጠናከርም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም