የአቶ መለስ ዜናዊ ሙት ዓመት ስንዘክር ስራዎቻቸውን ከዳር ለማድረስ ቃላችንን በማደስ ሊሆን ይገባል ---የትግራይ ክልላዊ መንግስት

138
መቀሌ ኢዜአ ነሐሴ 14/11 “የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሙት ዓመትን ስንዘክር የጀመሯዋቸውን ታላላቅ ስራዎች ከዳር ለማድረስ ቃላችንን በማደስ ሊሆን ይገባል” ሲል የትግራይ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ። የዝክረ መለስ ሰባተኛው ዓመት ምክንያት በማድረግ የክልሉ መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው አቶ መለስ ዜናዊ ከኢትዮጵያ አልፎው ለአፍሪካ ልማትና ብልጽግና መረጋገጥ ዘመን ተሻጋሪ ተግባር ፈጽመዋል። የክልሉ መንግስት “ የአቶ መለስ ዜናዊ ራዕይና ክብሮች የህዳሴያችን፣ የፅናታችንና የማይቀረው ድላችን ዋስትናና ነው ‘’ በሚል መሪ ሀሳብ በወጣው በዚሁ መግለጫው አቶ መለስ ኢትዮጰያን በአለም የተመሰከረለት የምጣኔ ሀብት እድገት እንዲመጣ የጎላ ሚና መጫወታቸውን አስታውቋል። በፖለቲካው ዘርፍም ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ አልፎ በዓለም መድረኮች የጎላ ተቀባይነት እንደነበራቸውም ተመልክቷል። አቶ መለስ ዜናዊ ይህንኑ ብቃት እንዲላበሱ ያደረጋቸው ጥልቅ ህዝባዊ ፍቅርና መሪ ድርጅታቸው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ/ህወሓት/ መሆኑ ተገልጿል። በችግር ትታወቅ የነበረችውን ሀገር በአዲስ የልማት፣ የሰላምና የዲሞክራሲ ጎዳና እንድትጓዝና በአለም መድረኮች ይበልጥ እንድትታወቅ  የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ተወስቷል። እንደመግለጫው አቶ መለስ “ የማይበገር የፅናት ተምሳሌት፣ በእውቀት የተመሰረተ አሸናፊነት የነበራቸውና ለሁሉም ነገር ዳኛው ህዝብ ነው “ የሚል የፀና አቋማቸው እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስ ሲሰሩበት ቆይተዋል። የልማት አርበኝነታቸው በተግባር ያስመሰከሩ፣ በህግ የበላይነትና በዓላማ ፅናት የሚያምኑ፣በትናንሽ ድሎች የማይኩራሩና ለህዝብ የነበራቸው ክብር በቀላሉ የማይረሱ የአቶ መለስ ልዩ የግል ባህሪያት መሆናቸውም ተገልጿል። የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት የሚኖሩባት ሀገር እንድትኖራቸው የሰሩ ታላቅ የህዝብ ልጅ እንደነበሩም ተገልጿል። በዚህ በጎ እና ታላቅ ተግባርም ሁሌም በህዝቦች ልብ እየታወሱ እንዲኖሩ የሚያደርጋቸው መሆኑም ተመልክቷል። “የአቶ መለስ ዜናዊ ሰባተኛ ሙት ዓመት ስንዘክር የህዳሴ ጉዞአችንን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማድረስ ቃላችንን ዳግም በማደስ ሊሆን ይገባል” ሲልም መግለጫው አውስቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም