በማይጨውና ሀዲሹ ከተሞች ጅብ በሰዎች ላይ ጉዳት አደረሰ

62
ማይጨው ኢዜአ ነሐሴ 14/11 በትግራይ ደቡባዊ ዞን በማይጨውና ሀዲሹ ከተሞች ጅቦች አምስት ሰዎችን በማጥቃት ጉዳት ማድረሱን ፖሊስ አስታወቀ። ጅቦቹ  ጉዳት ካደረሱባቸው ሰዎች መካከል ሶስቱ በማይጨው ቀሪዎቹ ደግሞ በአላጄ ሀዲሹ የሚኖሩ ናቸው። በሰዎቹ ላይ የደረሰው ጉዳት ከባድ ቢሆንም እስካሁን ግን ህይወቱ ያለፈ እንደሌለ የዞኑ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አዛዥ ኮማንደር ሐለፎም ሀዱሽ ለኢዜአ ገልጸዋል። በማይጨው ከተማ በጅብ ተነክሰው የተጉዱት ሰዎች ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ወደ ጸበል ለመሄድ በመጓዝ ላይ እንዳሉ ሲሆን በለምለም ካረል ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው። በወቅቱ በሶስት ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሰው ጅብ የጸጥታ አካላት ባደረጉት ትብብር መገደሉን ኮማንደሩ አመልክተዋል። በሀዲሹ ከተማ የተጎዱት ደግሞ ባለፈው እሁድ ምሽት አንዲት አዋቂ ሴት እና አንድ ህጻን ልጅ በከተማ በመንቀሳቀስ ላይ እንዳሉ ሲሆን በከተማ ጤና ጣቢያ ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል። ህብረተሰቡ ሌሊት ላይ በሚንቀሳቀስበት ጥንቃቄ እንዲያደርግም ኮማንደሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም