የአዘዞ ሁለገብ የገበያ ማዕከል ፕሮጀክት በመዘግየቱ ቅሬታ እንደገባቸው ነዋሪዎች ገለጹ

58
ጎንደር (ኢዜአ) ነሀሴ 14 ቀን 2011- በጎንደር ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኘው የአዘዞ ሁለገብ የገበያ ማዕከል ፕሮጀክት በመዘግየቱ ቅሬታ እንደተፈጠረባቸው የአዘዞ ፀዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። የፕሮጀክቱ የበላይ ተቆጣጣሪ የሆነው የጎንደር ከተማ ቤቶች ኮንስትራክሽን ልማት መምሪያ በበኩሉ የነዋሪዎች ቅሬታ ትክክል መሆኑን አምኖ ፕሮጀክቱን በማጠናቀቅ ለተጠቃሚው ለማስተላለፍ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል። ሁለገብ የገበያ ማዕከሉ በዓለም ባንክ የበጀት ድጋፍ የግንባታ ስራው በ2004 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ተጀምሮ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር። በአሁኑ ወቅትም ግንባታው ሙሉ በሙሉ ባለመጠናቀቁ በተገነቡ ህንጻዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ገልጸዋል። አስተያየታቸውን ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል አቶ አስማማው ጫኔ እንዳሉት በከተማዋ ዘመናዊ ንግድን ያስፋፋል ብለው ያሰቡት የገበያ ማዕከል ተጠናቆ ለአገልግሎት ባለመግባቱ ቅሬታ ገብቷቸዋል። ለከተማዋ ነዋሪዎች ከፍተኛ የሥራ እድል በመፍጠር፣ ለመንግስት ገቢ በማስገኘትና የከተማዋን ገጽታ በመቀየር የራሱ አስተዋጽኦ የሚኖረው የገባያ ማዕከል በአሁኑ ወቅት መስታወቱ በመሰባበሩና ኮርኒሱም በዝናብ መበላሸቱን አስረድተዋል። ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ረዚቃ አደም በበኩላቸው ማዕከሉ ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ቦታ ይሰጣል ብለው ተስፋ ቢያደርጉም ፈጥኖ ባለመጠናቀቁ ግቢው የቆሻሻ መጣያ መሆኑ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል። “የገበያ ማዕከሉ በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚሰራ በመሆኑ ችግሩ የአስፈፃሚው የትጋትና የልማት ተነሳሽነት ችግር መሆኑን ተገንዝበናል” ብለዋል፡፡ ሕንፃው መሰነጣጠቅ እንደጀመረ የገለጹት ወይዘሮ ረዚቃ፣ የከፋ ጉዳት ሳይደርስበት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ መንግስት ትኩረት ሊሰጥ የገባል ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸወዋል። ግንባታው እየተካሄደ ባለበት ቦታ የንግድ ሱቅ የነበራቸውና የተነሺዎች አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጌጡ እጅጉ በበኩላቸው ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ የግንባታ ወጭ ብቻ በመክፈል የሱቅ ተጠቃሚ ትሆናላችሁ በሚል ምንም ካሳ ሳይሰጣቸው ከቦታቸው እንደተነሱ አስታውሰዋል፡፡ እስከዛሬ ድረስ የገበያው ግንባታ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ባለመግባቱ በተሰጣቸው ጊዜያዊ ኮንቴነር ለመስራት መገደዳቸውን ጠቁመዋል። በቦታው የመኖሪያ ቤትን ጨምሮ በተለያዩ የንግድ ስራዎች የተሰማሩ ከ230 በላይ ተነሽዎች ችግር አለመፈታቱንም ጠቁመዋል። ለግንባታ ወጭ ክፍያ በዝግ ቁጠባ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አድርገው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል። የጎንደር ከተማ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ልማት መምሪያ የፕሮጀክቶች አስተባባሪ አቶ ታምራት ልዑልሰገድ በበኩላቸው በበጀት ችግር ምክንያት ግንባታው መጓተቱን አመልክተዋል። የገበያ ማዕከሉን ለማስገንባት ከ79 ሚሊዮን ብር በላይ በዕቅድ ቢያዝም እስካሁን ድረስ ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን ተናገረዋል። ቀሪ ስራዎችን እስከመስከረም ወር መጨረሻ በማጠናቀቅ ርክክብ ለማድረግና ለህብረተሰቡ ለማስተላለፍ ከኮንትራክተሩ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን አመልክተዋል። በግንባታ ላይ ያለው የገበያ ማዕከል ፈጥኖ ባለመጠናቀቁ ለጉዳት እየተዳረገ መሆኑን ህብረተሰቡ ያነሳውን ቅሬታ ትክክል መሆኑን አምነው፣ ተቋራጩ የማስተካከያ ስራ እንዲሰራ መነገሩንም ጠቁመዋል። ማዕከሉ ስድስት ብሎኮች ያሉት ሲሆን ሱቆችን፣ የእህል መጋዝን እና ወፍጮ ቤቶችን ጨምሮ 381 ክፍሎች እንዳሉት ተመልክቷል። በመምሪያው የመሰረተ ልማት ግንባታ ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ የኛነው አዲሱ በበኩላቸው ስድስት ህንጻዎች ያሉት የገበያ ማዕከሉ ለእህል መጋዘን፣ ለወፍጮቤትና ለሱቅ አገልግሎት የሚውሉ 381 ክፍሎች እንዳሉት ተናግረዋል። ከቦታው የተነሱ 273 ግለሰቦች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ተጠቃሚ ሲሆኑ ሌሎች 108 ሱቆችን ከተማው በሚያወጣው ጨረታ መሰረት ለተጠቃሚው እንደሚተላለፉ አመልክተዋል። በቦታው ለተነሱ ግለሰቦች ከማፍረሻ ወጭ የተሰጠን ካሳ የለም ቢሉም መምሪያው በወቅቱ በነበረው ጥናት መሰረት ካሳና ምትክ ቦታ መሰጠቱን አስታውሷል፡፡ “የገበያ ማዕከሉ ቅድሚያ ለተነሺዎች የተሰጠበት ሁኔታ ምትክና ካሳ አላገኙም በሚል ሳይሆን የተሰጣቸው ምትክ ቦታ የንግድ ቦታ ባለመሆኑ ነው፤›› ሲሉም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ የገበያ ቦታው የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማት አውታሮችን ጨምሮ በ7 ሺህ 360 ካሬ ሜት ቦታ ላይ ያረፈ መሆኑን ከመመሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም