ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ከተለመደው የአኗኗር ዘይቤ መውጣት ይገባል ተባለ

54
አዲስ አበባ ነሐሴ 14/2011 ካንሰርን ጨምሮ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጡትን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ውጤታማ ይሆን ዘንድ ህዝቡ የአኗኗር ዘይቤውን መለወጥ እንዳለበት የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ። ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የአመጋገብ ባህልንና ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ጨምሮ በአብዛኛው ከአኗኗር ዘይቤ ጋር በተያያዙ ጉድለቶች ሳቢያ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች መሆናቸው የመስኩ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ዓላማ ተብለው በተለያየ መንገድ የሚሰራጩ የግንዛቤ መፍጠሪያ መልዕክቶች ይዘትና መተላለፊያ መንገድ በጤና የተጠኑና ወጥነት ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይ የመከረ የባለድርሻ አካላት ውይይት ዛሬ ተካሂዷል። በሽታዎቹን ለመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ግንዛቤ ለመፍጠር ተብለው ባልተጠናና ወጥነት በጎደለው መንገድ የሚሰራጩ መረጃዎች የሚያሳስቱና ዜጎችን ለስጋት ጭምር ሊዳርጉ የሚችሉ ናቸው። በስብሰባው ላይ የጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ረዳት ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ንጉሱ እንደተናገሩት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ሰፊ ግንዛቤ መፈጠርና የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል ይገባል። በዚህ ረገድ በዜጎች ዘንድ ያለውን አመለካከት ለመቀየርና በሽታዎችን የመከላከል ተግባሩን ለማጠናከር ሚኒስቴሩ ከተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን አቶ ነብዩ ገልፀዋል። ከእነዚህም መካከል 'ከተሽከርካሪ እንቅስቃሴ የፀዳ ቀን' የሚለውን ወርሃዊ መርሃ ግብር ለአብነት አንስተዋል። ዜጎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴን የዘውትር ህይወታቸው አካል እንዲያደርጉ ተብሎ የሚካሄደው ይህ መርሃ ግብር በተለይ በከተሞች አካባቢ የእግር ጉዞ ባህል እየዳበረ እንዲመጣ እያገዘ መሆኑን ጠቅሰዋል። ዜጎች ማንነታቸው በውል በማይታወቁ አካላት በማህበራዊ ድረ-ገፆች ላይ የሚለጠፉ ህክምና ነክ መረጃዎችን ከመጠቀም በመቆጠብ የጤና ሚኒስቴር ለዚህ ብሎ ያዘጋጀውን ድረ-ገጽ እንዲጎበኝ አሳስበዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የካንሰር በሽታ የሚሰቃዩ ወገኖችን ህይወት ለመታደግ መንግስት  ሶስት ተጨማሪ የካንሰር ህክምና ተቋማትን መገንባቱንም ተናግረዋል። በጅማ፣ ሀሮማያና በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች የተገነቡት ማእከላቱ በአሁኑ ወቅት ገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም