በደቡብ ወሎ የዝናብ ውሃን በግድብ በማሰባሰብ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው

69
ደሴ (ኢዜአ) ነሀሴ 14 ቀን 2011- በደቡብ ወሎ ዞን የክረምቱን የዝናብ ውሃ በአነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ግድቦች በማሰባሰብ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የመስኖ ማህንዲስ ቡድን መሪ አቶ ኃይለሚካኤል ፈንታው ለኢዜአ እንደገለጹት የውሃ ማሰባሰብ ስራው እየተከናወነ ያለው በ20 ወረዳዎች ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶች ነው። ውሃ የማሰባስብ ሥራው በ49 አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ግድቦች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው ግድቦቹ ከ10 ሺህ እስከ 50 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት የክረምት ውሃን በማሰባሰብ ከ8 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉን ያስታወሱት አቶ ኃይለሚካኤል በተያዘው ክረምት ልምድና ተሞክሮን በመቀመር በስፋት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በነባር ግድቦች በሰኔ እና ሐምሌ ወር ደለልና ቆሻሻ የማስወገድ ስራ መሰራቱንና በአሁኑ ወቅትም ውሃ እንዲይዙ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል ። በተያዘው ክረምት ወደ አገልግሎት በገቡ 49 የመስኖ ግድቦች ላይ አዲስ ውሃ የማሰባሰብ ሥራ በዚህ ሳምንት መጀመሩን ገልጸው፣ ግድቦቹ ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ ለመስኖ ልማት ጥቅም እንደሚሰጡ ገልጸዋል። አቶ ኃይለማርያም እንዳሉት በመጪው የበጋ ወቅትም 20 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጭ ተጨማሪ ዘጠኝ ግድቦችን ለማስገነባት ታቅዷል። በተንታ ወረዳ የቀበሌ 13 ነዋሪ አርሶ አደር በላይ አንዳርጌ በበኩላቸው በአካባቢያቸው በተገነባ የመስኖ ግድብ በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ የቢራ ገብስ ማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ “ቀደም ሲል በበጋው ወቅት ያለ ስራ እናሳልፍ ነበር” ያሉት አቶ በላይ ገድቡ ከተገነባ በኋላ የክረምት ውሃ በማሰባሰብ አትክልት ፍራፍሬ በማልማት ኑሯቸውን ለማሻሻል መቻላቸውን ተናግረዋል። ሌላው በወረባቦ ወረዳ የቀበሌ 15 ነዋሪ አርሶ አደር ሐሽም አረቡ በበኩላቸው አካባቢያቸው በረሃ በመሆኑ ውሃ ለማግኘት ከሁለት ኪሎ ሜትር በላይ የእግር ጉዞ ለመሄድ ይገደዱ ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም በአካባቢያቸው በተሰራው ግድብ ከብቶቻቸውን በቅርበት ያለችግር ውሃ ማጠጣት ከመቻላቸዉ ባለፈ የቆላ ፍራፍሬ የማልማት ስራ መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ “ከግድቡ ደለል አፈርና ቆሻሻ በማስወጣት ሰሞኑን አዲስ ውሃ በማሰባሰብ ላይ ነን” ብለዋል፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን በየዓመቱ በመስኖ ከሚለማው ከ80 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም