አሜሪካ የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤል ማስወንጨፏ ተነገረ

189
ኢዜአ ነሃሴ 14/2011 አሜሪካ የመካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ ክሩዝ ሚሳኤል ሙከራ ማድረጓን በወታደራዊ መስሪያ ቤቷ ፔንታገን በኩል አስታውቃለች። ከሩሲያ ጋር አድርጋው የነበረውን የኒየክሌር ተሸካሚ መሳሪያዎች እቀባ ስምምነት አልተገብርም ካለች ከሳምንታት በኋላ ሚሳኤል መሞከሯ እያነጋገረ ነው።
ፔንታገን እንዳስታወቀው ባለፈው ዕሁድ በካሊፎርኒያ ዳርቻ የተሳካ የሚሳኤል ሙከራ አድርጓል። ሞስኮ በበኩሏ ዋሽንግተን ወታደራዊ ውጥረቱን እያባባሰችው ነው በሚል ድርጊቱን ኮንናለች። አሜሪካ ከመካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ የኒዩክሌር ባለቤት ኃይሎች ስምምነት በሩሲያ ተጥሷል በሚል በፈረንጆቹ 2019 ነሐሴ 2 ቀን ከስምምነቱ መውጣቷ ይታወሳል። ሩሲያ ከአሜሪካ የቀረበባትን የስምምነት መጣስ ውንጀላ አጣጥላለች። ተንታኞች የስምምነቱ ገቢራዊ አለመሆን አዲስ ወታደራዊ ፉክክርን ሊያመጣ ይችላል በሚል ስጋታቸውን ገልፀዋል። ከቀዝቃዛው ጦርነት ማግስት ተፈርሞ የነበረው ስምምነቱ ከ500 እስከ 5 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር የሚወነጨፉ ሚሳኤሎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እገዳ የጣለ ነበር ብሏል የቢቢሲ ዘገባ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም