የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የራስ መኮንን ሙዚየም ለጎብኝዎች ክፍት ሆነ

136
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 14/2011  ለዕድሳት ተዘግቶ የነበረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የራስ መኮንን አዳራሽ ሙዚየም ዕድሳቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ከዛሬ ጀምሮ ለጉብኝት ከፍት እንደሆነ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም አስታወቀ። ለሙዚየሙ ዕድሳት 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን የዕድሳት ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያና በጃፓን መንግስት መካከል በተደረገ ስምምነት የተካሄደ መሆኑ ታውቋል። የዕድሳት ስራውን በቅርስ ዕድሳት አለም አቀፍ ልምድ ባለው "ማፈርፒ" በተባለ ሃላፊነቱ የተወሰነ የጣሊያን የቅርስ ጥገና ስራ ተቋራጭ ኩባንያ መከናወኑን ለማወቅ ተችሏል። በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ የጥናትና ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታከለ መርዕድ እንደገለጹት፤ ሙዚየሙ ለ86 ዓመታት በላይ ያለ ጥገና አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት 'ገነተ ልኡል' በሚል የሚታወቀው ቤተ-መንግስት ለአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተሰጠ በኋላ ሙዚየም የሆነው የመኮንን አዳራሽ የተለያዩ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ይተላለፉበት እንደነበር ዶክተር ታከለ መርዕድ አስታውሰዋል። ሙዚየሙ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ሌሎች ተዛማጅ የትምህርት ተግባራት እየተከናወነበት እንደሆነም ገልጸዋል። ሙዚየሙ እንዲታደስ ያስቻለው በሙዚየሙ ውስጥ የሚገኙ ቅርሶችን ለትውልድ ጠብቆ ለማቆየትና ለጥናትና ምርምር እንደሆነ ተናግረዋል። የዕድሳት ስራው የተጠናቀቀው የራስ መኮንን አዳራሽ ሙዚየም ከዛሬ ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት ሆኗል። የቤተ መጻህፍት አገልግሎት ለመጀመር አስፈላጊ ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራ እየተከናወነ እንደሆነም ዶክተር ታከለ ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኬ ማትሱንጋ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ጃፓን 50 ዓመታትን የተሻገረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰው፤ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ አስተዳደር ጀምሮ ግንኙነቱ በወዳጅነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል። ሁለቱን አገሮች መንግስት ከመንግስት፣ ተቋማት ከተቋማት እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎችን ከዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተሳስር ዘርፈ ብዙ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል። የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ ይታወቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም