ኳታር ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት አጠናክራ መቀጠል እንደምትፈልግ አስታወቀች

65
ነሐሴ 13 ቀን 2011ኳታር ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት አጠናክራ መቀጠል እንደምትፈልግ የሀገሪቷ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማሃመድ ቢን አብድረህማን ቢን ጃዝሚን አልታሂኒ አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኳታሩን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማሃመድ ቢን አብድረህማን ቢን ጃዝሚን አልታሂኒን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። ውይይታቸውም በዋናነት የሁለቱ አገራት ግንኙነት በሚጠናከርበት ሂደት ላይ እንደነበር ነው የተገለጸው። አልታሂኒ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የዛሬው ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኳታርን በጎበኙበት ወቅት ከአገሪቷ ኢሚር ጋር የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር ያደረጉት ውይይት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለመነጋገር ነው። ኳታር ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ መቀጠል እንደምትፈልግም ጨምረው ገልጸዋል። የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በተለይም የሱዳንን ወቅታዊ ጉዳይ በተመለከተም ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል። የሱዳንን ወቅታዊ ችግር የሱዳናዊያንን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ለመፍታት የሚደረግ እንቅስቃሴን አገራቸው እንደምትደግፍም አስታውቀዋል። ኳታርና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመሩት በ1987 ዓ.ም. ሲሆን፤  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገራቱ  በትብብር ለመሥራት የሚያስችላቸውን የተለያዩ ስምምነቶችን መፈራረማቸው ይታወሳል። የኳታሩ ታዋቂ የቴሊቪዥን ጣቢያ  ‹‹አልጀዚራ›› በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም