የህንጻ አዋጁ በሚፈለገው ልክ ባለመተግበሩ ለእንግልትና ስቃይ እየተዳረግን ነው- አካል ጉዳተኛ ተገልጋዮች

44
ሚያዝያ 27/2010 በ2001 ዓ.ም የጸደቀው የህንጻ አዋጅ በሚፈለገው ልክ  ባለመተግበሩ ለእንግልትና ስቃይ  እየተዳረጉ መሆናቸውን አካል ጉዳተኛ ተገልጋዮች ተናገሩ፡፡ አቶ አስቻለው ተስፋዬ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱት በክራንች ቢሆንም ህይወታቸውን የሚመሩት ከንግድ ስራ በሚያገኙት ገቢ ነው፡፡ አብዛኞቹ ህንጻዎች እንደ እርሳቸው ላሉ አካል ጉዳተኞች ምቹ ባለመሆናቸው ጉዳያቸውን ለማስፈጸም እየተቸገሩ መሆናቸውን በምሬት ተናግረዋል፡፡ የተቋማት ባለሙያዎችና የስራ ኃላፊዎች ወደ መሬት ወርደው እንዲያናግሯቸው እስከመጠየቅ ቢደርሱም አገልግሎት ሰጪዎቹ ፈቃደኞች አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አሳንሰሮቹ ድረስ ያሉት የህንጻዎቹ ደረጃዎች መብዛትም አካል ጉዳተኞችን ለእንግልት እየዳረገ መሆኑን እራሳቸውን አብነት አድርገው አስረድተዋል፡፡ የዊልቼር  ተጠቃሚውና   የኢትዮጵያ  አካል ጉዳተኖች  ብሄራዊ   ማህበር ስራ  አስኪያጁ   አቶ ማሞ ተሰማ እንዳሉት ከህንጻ አዋጁ በኋላ ከተሰሩ ህንጻዎች ጥቂቶቹ ለአካል ጉዳተኞች እንቅስቃሴ ምቹ ቢሆኑም  አብዛኛዎቹ  ግን  ጉድለት   የሚታይባቸው ናቸው፡፡ በአዋጁ መሰረት በተሰሩ ህንጻዎችም ቢሆን ለአካል ጉዳተኞች መውጫና መግቢያ  የተዘጋጁ ራምፖች ደረጃቸውን የጠበቁ አለመሆናቸውና የአሳንሰሮች ጥበት በግልጽ የሚታዩ ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ማህበሩ  ችግሩን ለመቅረፍ ከኮንስትራክሽን  ሚኒስቴር፣ ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይና  ከሌሎች  ባለድርሻ  አካላት  ጋር  በቅርብት  እየሰራ መሆኑንም   አቶ  ማሞ  አብራርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበራዊ ችግሮች መከላከል ዳሬክተር አቶ ይድነቃቸው  ሃይሉ ችግሮች መኖራቸውን አምነው ከአስር አመታት ወዲህ  ከነችግሩም ቢሆን ተስፋ ሰጭ  ጅማሮ  መታየቱን ተናግረዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ደንቦች፣ ፖሊሲዎችና አዋጆች ወጥተው በመተግበር ላይ መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ ቢሮው ከህንጻ ዲዛይን፣ ከትምርት፣ ከጤና ተቋማትና  ከሌሎች ባለድርሻ  አካላት  ጋር ትስስር  ፈጥሮ   እየሰራ መሆኑን  አመላክተዋል፡፡ በአፈጻጸም ሂደት የሚፈጠረው ክፍተት ከግንዛቤ   እጥረትና   ከቸልተኝነት እንደሚመነጭ   ጠቅሰው የህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ የማሳደግ ስራዎች እንደሚሰሩም ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት፡፡ በኮንስትረክሽን  ሚኒስቴር  የኮንስትራክሽን  ህግጋት ዝግጅትና  አፈጻጸም  የደረጃዎች፣ ኮዶችና  እስታንዳርዶች  ዝግጅትና  ክትትል  ዳይሬክተር  ወይዘሮ  መዓዛ  ገብረአብእዝጊ  ለኢዜአ  እንዳሉት  የህንጻ አዋጁ ከ2003ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁ አዳዲስ በሚገነቡ ህንጻዎች ላይ መጠነኛ ለውጥ ቢያመጣም አዋጁን በተሟላ መልኩ በመተግበር ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን ነው ዳይሬክተሯ የገለጹት፡፡ ዳይሬክተሯ እንዳሉት ህንጻዎች በሚሰሩበት ወቅት ከዲዛይን ጀምሮ በአዋጁ የተካተቱ የውልቼር መሽከርከሪያ ራምፕ፣ አሳንሰር፣ የመወጣጫ ድጋፍ መካተት አለመካተታቸው ማረጋገጫ ይሰጥበታል፡፡ “የህንጻ አዋጁን የማስተግበሩ ሃላፊነት የከተሞችና የክልሎችም ነው” ያሉት ዳሬክተሯ ከ10 ሺ በላይ  ህዝብ  ላላቸው ከተሞች ህንጻ ሹሞች እንዲቋቋሙላቸው በማድረግ ክትትልና ድጋፍ እንደ ሚደረግ  አመላክተዋል፡፡ ወይዘሮ መዓዛ እንዳሉት የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሚኒስቴሩ ሰራተኛና ማህበራዊ  ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር ስምምነቶችን  ተፈራርሟል፡፡ በዘርፉ እውቀትና ልምድ ያለው የሰው ሃል እጥረት፣ በቁጥጥርና  ክትትል ላይ የሚታይ  ክፍተት፣ የግንዛቤ እጥረት፣ የባለሙያው የቁርጠኝነት ማነስ አዋጁ በሚፈለገው ልክ  ተግባራዊ  እንዳይሆን ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸው በጥናት መለየቱን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም