የቁሳቁስና የቦታ እጥረት በበጎ አድራጎት ስራዬ ላይ እክል ፈጥሮብኛል - ፍቅር ለነዳያን የበጎ አድራጎት ማህበር

75
ነሐሴ 13/ 2011 የቁሳቁስና የቦታ እጥረት የአቅሙን ያህል የበጎ አድራጎት ስራ እንዳያከናውን እክል እንደፈጠረበት ፍቅር ለነዳያን የተሰኘ በጎ አድራጎት ማህበር አስታወቀ። ማህበሩ ከተቋቋመ አንድ አመት ከሶስት ወር በላይ የሆነው ሲሆን፤ ለአረጋውያንና አካል ጉዳተኞች የንጽህና አገልግሎት እና የአልባሳት ድጋፍ ዘወትር እሁድ ያደርጋል። ማህበሩ የአልባሳት ድጋፍ የሚያደርገው ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በማሰባሰብ መሆኑን ገልጿል። እስካሁን ባለው ሂደትም ስልሳ የሚደርሱ በጎ ፈቃደኞች በማህበሩ ስር አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። የማህበሩ መስራች አቶ ገብረኪሮስ በላይ ሁለት ሰዎችን ለመርዳት አስበው ይህን በጎ ሰራ መጀመራቸውን ገልጸው፤ በጊዜ ሂደት መሰል ድጋፍ የሚሹ በርካታ አዛውንቶችን በመመልከታቸው  እርዳታውን ለመቀጠል መወሰናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል። ማህበሩ አገልግሎቱን የሚሰጥበት ቦታ ውስን በመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የአገልግሎት ፈላጊ አረጋውያን ቁጥር ማስተናገድ አለመቻሉንም አክለዋል። ማህበሩ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር አቅም የሌላቸው ዜጎችን ቤት በማደስ  እንደ አገር ለተደረገው የበጎ አድራጎት ጥሪ ምላሽ እየሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል።። ከማህበሩ ድጋፍ እያገኙ ከሚገኙት አረጋውያን መካካል የ70 ዓመቱ አቶ ኑሻጎ ተክለሃይማኖት ከዚህ በፊት ምንም አይነት የሚረዳቸውና የሚንከባከባቸው ቤተሰብ እንደሌለ ገልጸዋል። የማህበሩ አባላት ዘወትር  እሁድ ንጽህናቸውን እንደሚጠብቁላቸውና ልብሳቸውን እንደሚያጥቡላቸው ተናግረዋል። "የሚደረግልኝ ድጋፍ የቤተሰባዊነት ስሜት ፈጥሮብኛል" ብለዋል። የአካል ጉዳት ያለበት ወጣት ኤሊያስ አባዬ በበኩሉ ማህበሩ እንደልብ መንቀሳቀስ የሚያዳግታቸውን አካል ጉዳተኞች ማህበሩ እየደገፈ እንደሆነ ገልጿል። ፍቅር ለነዳያን የበጎ አድራጎት ማህበር የዘወትር ተግባሩን የሚከውነው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ጎጃም በረንዳ ተብሎ በሚባለው አካባቢ ድንኳን በመጣል ነው።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም