የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር ተመሰረተ

144
ነሐሴ 13/2011 የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር ዛሬ በይፋ ተመስርቷል። ማህበሩ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመረጃ ነጻነትና የመደራጀት መብቶች እንዲከበሩ የህግ፣ የፖሊሲና የማዕቀፎች እንዲሁም የአፈጻጸም ማሻሻያዎች እንዲስፋፉ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል። ጋዜጠኞች ከፖለቲካና ከንግድ ጥቅም ጫና ነጻ ሆነው እንዲሰሩ የሙያ ምህዳር ለመፍጠርና ከስራቸው ጋር በተያያዘ ከማንኛውም አካል ከሚሰነዘርባቸውን ጥቃት ለመከላከል ሙያዊ ብቃት እንዲሻሻልም እንዲሁ። ማህበሩ ዛሬ በአዲስ አበባ በይፋ ሲመሰረት ሰባት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎችም በአባላቱ ተመርጠዋል። ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎቹ መካከል ጋዜጠኛ ብሩህ ይሁንበላይ እንደገለጸው፤ የጋዜጠኞች የሙያ ማህበራት መመስረት ለኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ እድገት መሻሻል ጉልህ ሚና አለው። በተለይም ማህበራዊ ሃላፊነት የሚሰማው ሙያተኛና የሙያ ስነ-ምግባርና አሰራር የበለጠ እንዲስፋፋ አቅም ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታልም ብሏል። ብዝሃነትን የሚያንጸባርቁ የመገናኛ ብዙሃን በመላ አገሪቷ እንዲስፋፉና ሙያዊ አሰራር እንዲጎለብት ብሎም ነጻ፣ ገለልተኛና የታመነ የመረጃ ፍሰት አንዲኖር ለማስቻል እንደሚሰራም አብራርተዋል። ማህበሩ በቀጣይም ጋዜጠኞችና አርታኢያን የሙያ አቅማቸው እንዲጎለብት አቅም የሚገነቡ ትምህርቶችና ስልጠናዎችን መስጠት፣ ለዘርፉ የሚረዱ ጥናቶችን ማከናወንና የስነ-ምግባር ደንቦችን በማውጣት የሚሰራ ይሆናል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ማህበሩ የኢትዮጵያን የጋዜጠኝነት ሙያ ጥራት ከፍ የሚያደርግ መሆን አለበት። የመገናኛ ብዙሃንን ጥራት ለማምጣት ጋዜጠኞችና አርታኢያን ሙያው እንዲሻሻልና እንዲከበር በማድረግ ረገድ ያለመከፋፈል አንድ ሆነው መስራት እንድሚገባቸውም አሳስበዋል። ጋዜጠኝነት ትልቅ ፈተና የሚያጋጥመው የሙያ መስክ እንደመሆኑ በዘርፉ የሚገኙ ባለሙያዎች ፈተናዎችን ተቋቁመውና የሙያ ስነ-ምግባርን ተላብሰው ለህዝብ የሚገባውን ስራዎች መስጠት አለባቸውም ብለዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንም ሙያውን ለማሳደግና ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ወስጥ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል። በማህበሩ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ህግ መሰረት የተመዘገቡ የህትመትና የብሮድካስትንግ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ የሚሰሩ አርታኢያን በሙሉ አባል መሆን እንደሚችሉም ተጠቁሟል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም