''ለወጣቱ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ባለሃብቶች እናበረታታለን'' የድሬዳዋ ምክትል ከንቲባ

114
ድሬዳዋ ነሐሴ 13 / 2011 የድሬዳዋ አስተዳደር ሥራ አጥነትን ለማቃለል የሚደረገውን ጥረት ትርጉም ባለው መንገድ ለሚያግዙ ባለሃብቶች እገዛ እንደሚያደርግ ምክትል ከንቲባው አቶ አህመድ መሐመድ አረጋገጡ። በምክትል ከንቲባው የተመራው የአስተዳደሩ ካቢኔና የድሬዳዋ ኢህአዴግ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት አመራሮች በ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የተገነባውን ሬድዋ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡ አቶ አህመድ ከጉብኝቱ በኋላ በአስተዳደሩ ኢንቨሰትመንትን ለማሳደግና ሥራ አጥነትን ለማቃለል የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለሚያግዙ ባለሃብቶች ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡ ሬድዋ ሞተርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የገነባው መኪና መገጣጠሚያ ለወጣቱ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት አበረታች ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአስተዳደሩ ዘንድሮ 18 ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶችና ሥራ አጦች ሥራ ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንና ዕቅዱን ለማሳካት የባለሃብቱ ሚና ወሳኝነት እንዳለው አመልክተዋል፡፡ የሬድዋ ሞተርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደሰ አድማሱ አስተዳደሩ በሰጠው 42 ሄክታር መሬት ላይ ፋብሪካው በሁለት ዓመታት ውስጥ ተገንብቶ መኪና መገጣጠም መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር በቀን በሶስት ፈረቃዎች 450 ታታና ባለሦስት ጎማ ቲ ቪኤስ ተሸከርካሪዎች የመገጣጠም አቅም ቢኖረውም፣ በአሁን ሰዓት በተፈጠረው የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ሌሎች ችግሮች 30 ተሽከርካሪዎችን ብቻ እየገጣጠመ ነው ብለዋል፡፡ ድርጅቱ በድሬዳዋና በመላው አገሪቱ ባሉት 11 ቅርንጫፎቹ ከ1ሺህ 600 በላይ ሰዎችና በተለይም ለወጣቶች ሥራ መፍጠሩን አቶ ታደሰ አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ ታደሰ ገለፃ ፋብሪካው ለ15 ሺህ ሰዎች ከሚፈጥረው ሥራ ባሻገር ፤ ወደ ውጭ ከሚልካቸው ምርቶች በዓመት 183 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ያስገኛል፡፡ አስተዳደሩ ለኢንቨስትመት ሥራ የሰጣቸውን 116 ሄክታር መሬት ከይግባኝ ጥያቄ ነፃ አድርጎ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ‹‹ካሳ አልተከፈለንም አንወጣም ›› የሚሉ ቤተሰቦችም በሥራ ላይ ጫና እየፈጠሩ በመሆኑ አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡ ምክትል ከንቲባውና የአስተዳደሩ ካቢኔ አባላት ፋብሪካው ያጋጠሙትን ችግሮች በአጭርና በረዥም ጊዜ ለመፍታት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡ በፋብሪካው ሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ወጣት አማኑኤል ወንድወሰን በወር ከሚያገኘው ገንዘብ በተጨማሪ ‹‹የቀሰምሁት የቴክኖሎጂ እውቀት የትም ሄጄ መስራት እንድችል አድርጎኛል›› ብሏል፡፡ ''ሴት ወጣቶች በሁሉም የሥራ መስክ ውጤታማ መሆናችንን ለማረጋገጥ እኔ ምሳሌ ነኝ'' ያለችው ደግሞ ወጣት ትሁን ማሩ ናት፡፡ ''በተፈጠረልኝ የሥራ ዕድል ደስተኛ ነኝ። አስተዳደሩ ለእንደነዚህ ዓይነት ባለሃብቶች ድጋፍና እገዛ ቢያደርግ በርካታ ሥራ የሌላቸው ወጣቶች የሥራ ዕድል ያገኛሉ'' ስትልም ተናግራለች፡፡ ሬድዋ ሞተርስ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ እስካአሁን 19 ሺህ ተሽከርካሪዎች ገጣጥሞ ለገበያ ማቅረቡ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም