የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ

100
መቀሌ ሰኔ 6/2010 ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/  ማዕከላዊ ኮሚቴ   አስቸኳይ ስብሰባ  የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው ከሰኔ 3/2010 ጀምሮ ለሶስት ቀናት ያካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ  ሲያጠናቅቅ ያወጣው ባለዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡- I. መግቢያ፡- የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሰኔ 3-5 ያካሄደውን ኣስቸኳይ ሰብሰባ ኣጠናቋል። ህወሓት/ኢህወዴግ በ17 ዓመቱ የትጥቅ ትግልም ሆነ ሩብ ክፍለ ዘመን ባስቆጠረው የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ትግል ምዕራፎች ሁሉ ከሌሎች እህት ድርጅቶች ጋር በመሆን ባደረግነው ትግል በርካታ ድሎችን እየተጎናፀፍን እዚህ ላይ መድረስ ችለናል። የ43 ዓመታት የድልና የፅናት ጉዞአችን ስኬት ምንጭ የጠራና ብቁ አብዮታዊ መስመር ይዘን የዘለቅን መሆኑ ነው። ይኸንን መስመር በፅናት ጨብጦ በፅናት ታግሎ የሚያታግል ድርጅት ባለቤት ስለሆንን ነው። ባለፉት 27 ዓመታት ባጠቃላይ፣ ባለፉት 17 የተሐድሶ ዓመታት ደግሞ በተለይ ዙርያ መለስ መሰረታዊ ለውጥ ማስመዝገብ ችለናል። አገራችን ኢትዮጵያ የነበረችበት እጅግ ኣስፈሪ የመበታተንና የማሽቆልቆል ጉዞ ተገቶ ወደ ኣዲስ ምዕራፍ እንድትሸጋገርና ስምና ክብሯ ከፍ ብሎ እንዲጠራ ኢህኣዴግ እልህ አስጨራሸ ትግል ኣካሂዷል።በተደረገዉ ትግል የአገራችን ህዝቦች የመልማት እኩል ዕድል ያረጋገጠ ስርዓት ተገንብቶ ህዝቦችን በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ረገድ ተጠቃሚ ማድረግ የስቻለ ዉጤት ለማረጋገጥ ተችሏል። በእርግጥም አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችን አገራችንን ከጥፋት የታደገ፣ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት የተረጋገጠባት አዲሲቷ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ያደረገና ለወዲፊትም የአገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ ብቸኛው መንገድ መሆኑ የእስከኣሁኑ ትግላችን ያረጋገጠው እውነት ነው። ተአምር የፈጠረውና የአገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ የሚያስችለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አደጋ ውስጥ የወደቀበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ እንዲፈጠር ከምንም በላይ የመሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ አመራር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ባህሪው እየተሸረሸረ በከፋ የጥገኛ ዝቅጠት አረንቋ ውስጥ በመዘፈቁ መሆኑን ድርጅታችን ኢህአዴግ በሚገባ የተነተነው ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ ይህን ፈተና በሚገባ ለማለፍ ሲባል ድርጅታችን የጀመረው በጥልቅ የመታደስ እንቅስቃሴ ኣሁንም ቢሆን በሚፈለገው ደረጃ ሊሳካ አልቻለም። ይህንን መነሻ በማድረግ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ በወሰናቸው ውሳኔዎች በአገራችንና ክልላችን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በቀጣይ የትግል አቅጣጫዎቻችን ላይ በዝርዝር በመውያየት ውሳኔዎችን አስልፏል። IIውሳኔዎች ሀ. የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ግንቦት 28/2010 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ሰብሰባ የኢትዮ-ኤርትራን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና የመንግስት የልማት ድርጅቶችን አስመልክቶ በህወሓት ስራ አስፈፃሚ የቀረበለትን ሪፖርት በዝርዝር በማየት የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል።
  1. ከምንም ነገር አስቀድሞ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ሊያየው ይገባ የነበረው ጉዳይ የኢህአዴግ ምክርቤት በመጋቢት 2010 ዓ.ም ያስቀመጠውን ወሳኔና ግምገማ መሰረት በማድረግ በድርጅታችን በግልጽ እየታየ የመጣውን መሰረታዊ የአመራር ብልሽትና ያስከተለውን ጉዳት፤ እንዲሁም ባለፈው የተጀመረው በጥልቀት መታደስ የደረሰበትን ደረጃ በጥልቀት በመገምገም በአገራችን ዋነኛ ችግር ላይ ትኩረት አድርጎ ማየት አለመቻሉ አንድ መሰረታዊ ጉድለት ነው።
2.የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ማየት የነበረበት ሌላ መሰረታዊ ጉዳይ አሁን እየገጥመን ላለው መሰረታዊ የኢኮኖሚ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ ላይ ትኩረት አድርጎ መወያየት መሆን ሲገባው ችግሩ ባስከተላቸው ውጤቶችና ለጊዜያዊ መፍትሔዎች ቅድሚያ መስጠቱ አንድ ሌላ ጉድለት እንደሆነና፣ ዘላቂው መፍትሔ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመራችን በግልፅ የለያቸውን የልማት አቅሞቻችን ማለትም መላው ህዝባችን፣ መንግስትና የግል ባለሃብቱን በማደራጀት ርብርብ እንዲያደርጉ መቻል ላይ ያለብን ችግር ላይ ትኩረት ስጥቶ መውያየት አልቻለም።
  1. እነዚህ ጉድለቶች እንደ ተጠበቁ ሆነው ስራ አስፈፃሚው የኢትዮዽያና የኤርትራን ጉዳይ አስመልክቶ የወሰነው ውሳኔ በመሰረቱ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም በአጠቃላይ ለሁለቱ አገራት ወንድማሞች ህዝቦች በተለይ ሲባል ስምምነቱን ያለቅድመ ሁኔታ በመቀበል ህዝባችንና መላው አበላችንን በማወያየትና በማሳመን እንዲሁም ዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ ከጎኑ በማሳለፍ ለተግባራዊነቱ ያላሰለሰ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች ላለፉት 18 ዓመታት ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ አልተቻለም።ስለሆነም የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያሳለፈው ውሳኔ በመሰረቱ ከሰላም ፖሊስያችን ጋር የተጣጣመ መሆኑን በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ውሳኔ መተላለፉ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ደምድሟል።
ኣፈፃፀሙን በሚመለከት ግን ሃገራችን ከሌሎች ጎረቤት ሃገራት ጋር ካሏት የአዋሳኝ ድንበር ጉዳዮች አንፃር ጭምር እጅግ ከፍ ያለ ትርጉም ያለዉ በመሆኑ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊታይ እንደሚገባዉ አፅንኦት ሰጥቶ ተወያይቷል። ከዚህ ጋር በተያየዘ በኢትዮ-ኤርትራ አዋሳኝ አከባቢዎች የሚኖረዉ ህዝብና ሚሊሻ ላለፉት 20 ዓመታት ከኑሮኣቸዉና ከሥራቸው ተፈናቅለዉ የሃገራችንን ሉዓላዊነትና ህገ-መንግስታችንን ለማሰከበር ከመከላከያ ሰራዊታችን ጎን በመቆም ላሳዩት ቁርጠኝነትና ለከፈሉት የማይታመን መስዋዕትነት የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ያለዉን ክብርና ኣድናቆት እየገለፀ ድርጅታችን ኢህአዴግ ከፌደራል መንግስት ጋር በመሆን በቂ ድጋፍ ሊያገኙ እንዲሚገባ ወስኗል።
  1. የኢህኣዴግ ስራ ኣሰፈፃሚ ኮሚቴ አሁን የገጠመንን ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመፍታት እንዲቻል ከመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል ቴሌ፣ ኤለክትሪክ ማመንጫዎች፣ ሎጀስቲክስና የኢትዮዽያ ኣየር መንገድ ከፍተኛዉን ድርሻ በመያዝ የግል ባለሃብቶችን ለማሳተፍ እንዲሁም የቀሩትን የልማት ድርጅቶች በከፊል ወይም በሙሉ ወደ ግል ይዞታ ለማስተላለፍ የወሰነዉ ውሳኔ ከፕሮግራማችንና ፖሊስዎቻችን ጋር የማይጋጭ፣ ባለፉት ጉባኤዎቻችን እየተወሰነ የመጣና ወቅታዊ መሆኑን በማረጋገጥ ተቀብሎታል። ይሁን እንጂ ኣፈፃፀሙ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግና ልማታዊ ዴሞከራሲያዊ መስመራችንንም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ መከናወን እንዳለበት አፅንኦት ሰጥቶታል።
  2. በኢትዮ-ኤርትራ ዘላቂ ሰላም ጉዳይም ሆነ ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ጋር በተያያዘ የተወሰኑ ውሳኔዎች ወደ ኢህአዴግ ምክርቤት ሳይቀርቡ፣ አጋር ድርጅቶች ሳይሳተፉበት እና የሚመልከታቸው አካላት በዝርዝር ሳይወያዩበት እንደመጨረሻ ውሳኔ ተወስዶ ለህዝብ ይፋ መደረጉ አንድ ጉድለት እንደሆነ ማእከላዊ ኮሚቴዉ ደምድሟል።
  3. የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከዳር እስከዳር በከፍተኛ ሃገር ፍቅር የተሳተፉበት እና መስዋእት የከፈሉበትን ጉዳይ በዝርዝር ሳይወያዩበት እና በቂ መተማመን ሳይደረስበት በሚድያ ይፋ መግለጫ መሰጠቱ ህዝባችን ላይ ቅሬታ፣ ቁጣና መደነጋገር የፈጠረ መሆኑም አንድ ሌላ ጉድለት ነው።
ለ. የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ በጥልቀት ከተወያየባቸው ጉዳዮች አንዱ አሁን ያለንበት ክልላዊ እና ሃገራዊ ሁኔታ እንዲሁም ቀጣይ የትግል አቅጣጫዎች የሚሚለከት ነው። በኢህኣዴግ ደረጃም ሆነ በህወሓት ካለፉት አመታት ጀምሮ ልማታዊ መስመራችን እና በህገመንግስታችን ላይ እያጋጠመ ያለዉን ችግር ሲገመግም ቆይቷል። ይሁን እንጂ የችግሮቹ ስፋትና ትርጉም በኢህአዴግ ደረጃ በጥልቀት መገምገም እንዳለበት በመግባባት ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል።
  1. የኢህአዴግ ምክርቤት በመጋቢት 2010 ባስቀመጣቸው ውሳኔዎች ድርጅታችንን ከአደጋ ለማዳን እንዲቻል የለየናቸው ችግሮች እና መፍትሔዎቻቸው በጥብቅደዲስፕሊን እና ተጠያቂነት እንዲተገበሩ ግልፅ አቅጣጫ አስቀምጧል። በዚህ ረገድ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴው የደረሰበት ደረጃ በኢህአዴግ እንዲገምገም የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ይጠይቃል።
  2. በዴሞክራሲ ሓይሎች እና በጥገኝነት መካከል የሚደረገው ቀጣዩ የትግል ምእራፍ በዋናነት በዴሞክራሲ እና በልማት ዙርያ በሚለኮስ ንቅናቄ ማሕበራዊ መሰረታችን እና ከልማታችን ተጠቃሚ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሚያደርጉት የተደራጀ ትግል ነው። ይህን ለማድረግ እንዲቻል መላው ህዝባችን እና አባላችን የምንገኝበትን መድረክ ባህሪ መነሻ በማድረግ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ በሃገር ደረጃ በሚደረገው ሁሉንአቀፍ ትግል በቁርጠኝነት እንዲረባረብ ወስኗል።
  3. በአሁኑ ወቅት በኢህአዴግ ደረጃ እየተደረጉ ያሉ የኢህአዴግን ህገ-ደንብ እና ተቋማዊ አስራር ያልተከተሉ የአመራር ምዳባዎች እንዲታረሙ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ይጠይቃል።
  4. ለድርጅታችን ነባር አመራሮች እውቅና እንዲሰጥ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ወስኗል።
  5. በሃገራችን ህገ መንግስት በሚገባ መልስ የተሰጠባቸው የማንነት እና የወሰን ጥያቄዎችን ፌደራላዊ ስርዓታችንን በመፃረር እና የህዝባችን ክብር በሚነካ መልኩ በሓይል እና በተፅእኖ የትግራይን ህዝብ አንድነት እና ሰላም ለመረበሽ እየተደረጉ ያሉት ፀረ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችን ህወሓት ከህዝቡ ጋር በመሆን በፅናት ለመታገል ወስኗል።
  6. የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ የአብያታዊ ዴሞከራሲያዊ መስመራችን አስተማማኝ ደጀን በመሆን ትግላችንን የሚያጠናክር እና እንደ ካሁን ቀደሙ በመሰመራችን ዙርያ ጠንካራ ርብርብ እንዲደረግ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ወስኗል።
  7. ከህዝባችን ጋር ባለፉት ጥቂት ወራት ባካሄድናቸው መድረኮች በርካታ ችግሮች እንዳሉ ተገንዝበናል። ድርጅታችን የነዚህ ችግሮች መነሻ እንዲሁም የመፍትሔ ኣቅጣጫ በግልፅ ኣስቀምጦ በተግባር ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ሌት ተቀን ርብርብ ለማድረግ ወስኗል።
  8. ህዝባችን መሪ ድርጅቱ እንዲታደስ በተለያዩ መድረኮች ያደረገዉ ተሳትፎ እና ትግል ልማታዊ እና ዴሞክራሲያዊ ባህሪውን ጠብቆ እንዲሄድ ላደረገው አስተዋፅኦ ማእከላዊ ኮሚቴው አድናቆቱን እየገለፀ፤ በቀጣይም ቢሆን ትግሉን በተደራጀ መልኩ እንዲቀጥል ጥሪውን ያቀርባል። በዚህ አጋጣሚ ሰላማዊ እና ህጋዊ መንገድ ተከትለው ኣማራጭ ሃሳብ ከሚያራምዱ ሓይሎች ጋር ኣብሮ ለመስራት ያለውን ዝግጁነት መግለፅ ይወዳል። ይሁን እንጂ ህወሓት እና የትግራይን ህዝብ ለማዳከም እና ለመምታት በተለያዩ መንገዶች ፀረ ትግራይ ህዝብ እና ፀረ ህወሓት እንቅስቃሴ የሚያድርጉ የውስጥም የውጭም ሓይሎችን ህዝቡ ኣምሮ እንዲታግላቸው የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል።
  9. ወቅታዊ ሁኔታዉን በፍጥነት ለማየት እና ለመገምገም የኢህኣዴግ ስራ አስፈፃሚ እና ምክርቤት አስቸኳይ ሰብሰባ እንዲጠራ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ይጠይቃል።
ህገ መንግስታችና ህገ መንግስታዊ ስርአታችን ለማጠናከር እንረባረብ!! ዘለአለማዊ ክብርና ሞገስ ለትግሉ ሰማእታት!! የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ሰኔ 06/2010 ዓ.ም መቐለ፤
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም