የአገር አቀፉ የኮፓ ኮካ ኮላ የታዳጊ የእግር ኳስ ውድድር ከሁለት ሳምንት በኋላ ይጀመራል

63
አዲስ አበባ ሰኔ 6/2010 ለሶስት ወራት የሚካሄደው አራተኛው አገር አቀፍ የኮፓ ኮካ ኮላ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር ከሁለት ሳምንት በኋላ ይጀመራል። በውድድሩ በመላው አገሪቱ እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች መካከል የሚደረግ ሲሆን በውድድሩ ላይ ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 2 ሺህ 500 ቡድኖች የታዳጊ ቡድኖች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። በአጠቃላይ በውድድሩ ላይ 45 ሺህ ታዳጊዎች ይሳተፋሉ የተባለ ሲሆን በውድድሩ ላይ የሚሳተፉት ታዳጊዎች ከትምህርት ቤቶች የተመለመሉ ናቸው። ኮካ ኮላ፣ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በመተባበር ውድድሩን እንደሚያዘጋጁት ተገልጿል። የውድድሩ አዘጋጆች ዛሬ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ውድድርን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የኮካ ኮላ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ የብራንድ ስራ አስኪያጅ ወይዘሪት ትዕግስት ጌቱ  ''የእግር ኳስ ውድድሩ ብቃት ያላቸውን ታዳጊ ወጣቶች ለማፍራት የሚያግዝ ነው'' ብለዋል። በባለፉት ሶስት ውድድሮች የተሳተፉ ወደ 100 የሚጠጉ ታዳጊዎች ወደ ኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ መግባታቸውን ተናግረዋል። በዚህ ዓመትም ጥሩ የእግር ኳስ ክህሎት ያላቸው በርከት ያሉ ታዳጊዎች እንደሚታዩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በቀጣይ ዓመታት ለብሔራዊ ቡድን መጫወት የሚችሉ በርካታ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ከውድድሩ ለማፍራት እቅድ መያዙን ነው ወይዘሮ ትዕግስት ያስረዱት። በሁሉም ክልሎችና ከተማ በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ውድድሮች በማካሄድ በሁለቱም ጾታዎች 11 ቡድኖችን በመለየት የማጠቃለያ ውድድር ለአንድ ሳምንት በሃዋሳ ከተማ በማካሄድ አሸናፊው እንደሚለይ ተገልጿል። አገር አቀፍ የኮፓ ኮካ ኮላ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር በ2007 ዓ.ም ሲጀመር 2ሺህ ታዳጊዎች በማሳተፍ የተጀመረ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሳታፊ ቁጥሩን በማሳደግ በዘንድሮው ዓመት 45 ሺህ ታዳጊዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም