በመቀሌ ከተማ የሴቶች 5ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድር ተካሄደ

52
መቀሌ (ኢዜአ) ነሐሴ 12 ቀን 2011ዓ.ም- የአሸንዳ በዓልን ምክንያት በማድረግ በመቀሌ ከተማ የሴቶች 5ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድር ተካሄደ። በዚህ ውድድር ታዋቂ ሴት አትሌቶች፣ የከተማው ነዋሪ ሴቶችና ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል። በውድድሩ አትሌት ገነት ሳሀለ ከእንደርታ፤ አሰፉ አብርሃ ከትራንስ ኢትዮጵያ፤ ማርታ ፀጋይ ከጉና ክለቦች ተከታትለው በመግባት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ወጥተዋል። ለውድድሩ አሸናፊዎቹ እንደ ደረጃቸው የአስር ሺህ፣ የአምስትና የ2ሺህ 500 ብር ሽልማት የተበረከተ ሲሆን ለሁሉም ተሳታፊዎች ሜዳሊያ ተሰጥቷል። በሩጫ ውድድሩ ላይ የተሳተፈችው ወጣት ስምረት ካልአዩ ውድድሩ ለሴቶች በተለየ ሁኔታ መዘጋጀቱ ሴቶች በስፖርት ያላቸውን ተሳትፎ እንደሚያሳድገው ተናግራልች። በባህላዊና መንግስታዊ በዓላት ተመሳሳይ ውድድሮች ቢዘጋጁ ከቱሪዝም መስህብነቱ አልፎ የህብረተሰቡን ጤና በመጠበቅ በኩል ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ትዕግስት አለሙ ናቸው። “አሸንዳ ለአንድነታችን፣ ለሰላምና ለቱሪዝም ዕድገት የምናከብረው በዓል ነው” ያሉት ደግሞ የትግራይ ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርኽቲ ገብረመድህን ናቸው። ልጃገረዶችና ሴቶች በዓሉን ሲያከብሩ ባህላዊ አልባሳት፣ መዋቢያዎችና ጌጦችን በመጠቀም ማክበር እንዳለባቸው ተናግረዋል። የትግራይ ክልል ሴቶች ቢሮ ኃላፊ ዶክተር የትምወርቅ ገብረመስቀል በበኩላቸው በሩጫ ውድድሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት “አሸንዳ ከማይዳሰሱ ታሪካዊ ቅርሶች አንዱ በመሆኑ የዘፈኖች ግጥምና ዜማ ሳይበረዙ ባህላዊነቱ ተጠብቆ መጫወት ይገባናል” ብለዋል። በዓሉን በቱሪዝም መስህብነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስመዝገብ በሚደረገው እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚገባም አመልክተዋል። የሩጫ ውድድሩ አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገበረማርያምና አትሌው ወርቅነሽ ኪዳነ ከወጋገን ባንክና ከትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ማዘጋጀታቸው ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም