የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የመረጃ ተደራሽነት ችግር አለባቸው

61
አዲስ አበባ ሰኔ 6/2010 የመንግስታዊ ተቋማት ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች መንግሥትና ሕዝብ ከሚፈልገው አኳያ የመረጃ ተደራሽነት ችግር እንዳለባቸው ተገለጸ። የፌዴራል መንግስት ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የጋራ ፎረም ዛሬ በቢሾፍቱ ተካሂዷል። በፎረሙ ላይ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎቹ የአገሪቱ ሕዝብና መንግስት ከሚፈልጉት አኳያ መረጃን ተደራሽ የማድረግ ችግር እንዳለባቸው ተመልክቷል። በየተቋማቱ ያሉ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የእኔነት መንፈስ አለመኖርና አመራሮች ለዘርፉ የሰጡት ትኩረት አናሳ መሆን የመረጃ ተደራሽነቱን ችግር ያለበት እንዳደረገው ተጠቁሟል። በየተቋማቱ ባሉ ባለሙያዎች ላይ የሚስተዋለው የመፍራትና ጉዳዮችን ወደሌሎች የማስተላለፍ ዝንባሌ ለዘርፉ ችግር መፈጠር ምክንያት መሆኑም ተነስቷል። ባለሙያዎቹ በወቅታዊ ጉዳዮች ብቻ መጠመድ፣ የተቋማቱን የስራ አፈጻጸም በሚመለከት ግድፈቱንና ስኬቱን ሚዛናዊ በሆነ አግባብ ለኅብረተሰቡ አለማቅረብ፣ ከሚዲያ ጋር ተቀናጅቶ አለመስራትና ለሚዲያዎችም መረጃ የመስጠት ችግሮች በባለሙያዎች ላይ ይስተዋላሉ ተብሏል። የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች በአንድ ጀምበር እንደማይፈቱ ገልጸው፤ የአቅም ግንባታና የአደረጃጅት መዋቅራዊ ለውጥ ላይ በስፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል። በዘርፉ ላይ ጥረቶች ቢኖሩም አገሪቱ ከምትፈልገው አንጻር ሰፊ ክፍተት እንዳለ ጠቅሰው፤ ወደፊት ባለው አቅም ተጠቅሞ ይበልጥ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል። የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎቹ ማህበራዊ ሚዲያን እንደ አማራጭ በመጠቀም መረጃን በፍጥነትና በተደራጀ አግባብ ለህብረተሰቡ ሊያደርሱ እንደሚገባ አሳስበዋል። ባለሙያዎቹ የክህሎት ክፍተትና የተቋም አመራሮች ድጋፍ ችግር ያለባቸው በመሆኑ በሚፈለገው ልክ በመረጃ ተደራሽ ባለመሆን በቂ የሆነ የህዝብ ግንኙነት ስራ መስራት አለመቻላቸውን ተናግረዋል። በዘርፉ የሚፈለገውን ስራ ለመስራት እንዲቻል ከአደረጃጀት፣ ከክህሎትና ከተቋም አመራሮች ጋር በተያያዘ የሚነሱ የባለሙያው ጥያቄዎች በመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በኩል ትኩረት ተሰጥቶት ሊመለስ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም