በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው የፌዴራል መንግስት መደበኛ ገቢ ከ85 በመቶ በላይ መሰብሰቡ ተገለፀ

48
ነሐሴ 11/2011 በ2011 በጀት ዓመት ከፌዴራል መንግስት መደበኛ ገቢ ይሰበሰባል ተብሎ ከታቀደው 380 ቢሊዮን ብር ከ326 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ። የገንዘብ ሚኒስቴር የ2011 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀሙን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ እንዳሉት በበጀት አመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው ገቢ 85 ነጥብ 84 በመቶ ማሳካት ተችሏል። በዋነኛነት የበጀት ምንጩ የታክስ ገቢ መሆኑን ተናግረው ከታክስ ገቢ 213 ቢሊዮን በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ 176 ቢሊዮን በላይ መሰብሰብ መቻሉንም ገልፀዋል። በ2012 በጀት ዓመት የታክስ ሪፎርሞች ለማሻሻል 8 መመሪያዎች ተዘጋጅተው ወደ ስራ ተገብቷል። መመሪያዎቹ ሲተገበሩ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ የተሻለ ገቢ መሰብሰብ እንደሚቻል እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። አዋጭነታቸው ለተለዩ ፕሮጀክቶች ብቻ ብድር እየተወሰደ መሆኑን የገለጹት  አቶ ሀጂ በበጀት አመቱ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር ሀገሪቷ መበደሯን ጠቅሰዋል። ብድሩ በረጅም ጊዜና አነስተኛ ወለድ የሚከፈል እንደሆነም አስረድተዋል። በበጀት አመቱ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ከወጪ ንግድ መገኘቱን ጠቅሰው ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 177 ሚሊዮን ዶላር ወይም 7 በመቶ ያህል ቅናሽ ማሳየቱን ገልፀዋል። ከጥራጥሬ፣ ጫትና ጨርቃጨርቅ የተገኘው ገቢ ጭማሪ ከማሳየቱ በስተቀርሪ የኤክስፖርት አፈፃፀሙ በዋና ዋና ምርቶች ላይ ቀንሷል ብለዋል። በበጀት ዓመቱ ከ102 የፌዴራል ባለበጀት መስሪያቤቶች እየተካሄዱ ላሉ 1 ሺህ ፕሮጀክቶች የፕሮጀክት መግለጫ መዘጋጀቱንም አብራርተዋል። የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በተመለከተ በበጀት ዓመቱ ለመክፈል ከታቀደው 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መከፈሉንና ይህም የእቅዱ 97 በመቶ መከናወኑን አስርድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም