ሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገዶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን አሳድገውልናል-የትግራይ ማዕከላዊ ዞን አርሶ አደሮች

69
አክሱም ነሐሴ 11 / 2011 በትግራይ ማዕከላዊ ዞን አርሶ አደሮች ሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገዶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን አሳድገውልናል አሉ። አርሶ አደሮቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት መንገዶቹ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የነበሩባቸውን ችግሮች አቃለዋቸዋል። መንገዶቹ በተለይ እርሻን ለማዘመንና የግብርና ግብአቶችን ለማጓጓዝና ምርቶቻቸውን በቀላሉ ለመሸጥ እንዳስቻሏቸው አስታውቀዋል። የናዒደር ዓዲት ወረዳ ጨሞ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ተስፋይ ዘርኡ ከትውልድ ቀያቸው ወደ ዋና መንገድ የሚያገናኝ መንገድ በመገንባቱ ዘመናዊ ማዳበሪያን በወቅቱ አጓጉዘው ለመጠቀም አስችሏቸዋል። ከቀበሌያቸው በወሊድ ጊዜ ምጥ የተያዙ እናቶችን ወደ ሕክምና ተቋም ለማድረስ ስንቸገር ነበር ያሉት አርሶ አደሩ፣አሁን መንገድ በመሰራቱ ወላዶችን ወደ ሕክምና ተቋም በቀላሉ ለማድረስ እንደተቻለ ገልጸዋል። የዚሁ ወረዳ ሌላዋ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር መብሪሂት ገብረተንሳይ መንገዶች በመገንባታ ምክንያት ግማሽ ሰዓት ባልሞላ ጊዜና በፈለጉት ከተማ በተሽከርካሪ ተጉዘው ምርቶቻቸውን በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ። ቀደም ሲል የግብርና ምርቶቻቸውን ወደ አክሱምና ሌሎች ከተሞች አጓጉዘው ለመሸጥ የስድስት ሰዓታት የእግር ጉዞ ለማድረግ ይገደዱ እንደነበር በማስታወስ። የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጸጋይ ገብረ ኪዳን እንዳሉት የዞኑን 52 የገጠር ቀበሌዎችን እርስ በእርሳቸውና ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር የሚያገናኙ 234 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገዶችን ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አስታውቀዋል። በመንገዶቹ ግንባታ ከ71ሺህ በላይ የዞኑ አርሶ አደሮች የጉልበት ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ለአገልግሎት በበቁት መንገዶችም አርሶ አደሮች የግብርና ግብዓቶችን ገዝተው ለመጠቀምና ምርቶቻቸውን በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ እንዳደረጉላቸው አቶ ጸጋይ አመልክተዋል። መንገዶቹ የአርሶ አደሮቹን ማህበራዊ ግንኙነት አጠናክረውታል ብለዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም