በጎዳና ላይ የሚኖሩ ህጻናትን ለመታደግ በሚደረገው አገር አቀፍ ንቅናቄ የሀይማኖት መሪዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ ተጠየቀ

2747

አዲስ አበባ  ሰኔ 6/2010 የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ በጎዳና ላይ የሚኖሩ ህጻናትን ለመታደግ በሚደረገው አገር አቀፍ ንቅናቄ በየደረጃው የሚገኙ የሀይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑ ጠየቀ።

ጉባኤው በአገር አቀፍ ደረጃ ለ25ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአፍሪካ ሕፃናት ቀን አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንደተገለጸው ሕፃናትን ከጎዳና መታደግ የሞራል ብቻ ሳይሆን ከሀይማኖትም አንጻር የሚያስፈልግ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል።

የሀይማኖት ተቋማት ምዕመናን ለችግሩ ትኩረት እንዲሰጡና ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ማስተማር እንደሚገባ ጉባኤው አሳስቧል።

ከቤተሰቦቻቸውና ከአሳዳጊዎቻቸው ቁጥጥር ወጥተው ኑሮአቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ህጻናትና ታዳጊ ወጣቶች ለድርብርብ ችግሮች፣ ለህገ ወጥ ባህሪና ለወንጀል ተግባራት ይጋለጣሉ።

እነዚህን ሕጻናት ለመታደግ በመንግስት በኩል መልካም ጅምሮች ቢኖሩም ከችግሩ ስፋትና የሚፈለገውን ውጤት ከማምጣት አንጻር የሁሉም አስተዋጽኦ ያስፈልጋል ተብሏል።

ሕፃናትን ከጎዳና ሕይወት ለመታደግ ሁሉም ወገን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተገልጿል።

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የገነቡትን የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል በማስቀጠል “ሕፃናትን እንታደጋቸው”  በማለት ጉባዔው ጥሪ አቅርቧል።