በትግራይ የኤሊኖ ክስተትን ለመቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው

123
መቐለ ኢዜአ ነሐሴ 11/2011 በኤሊኖ ምክንያት የዝናብ እጥረትና መቆራረጥ በተከሰተባቸው አከባቢዎች የዝናብ ውኃ የመያዝና ጎርፍ የመቀልበስ ስራዎችን በተጠናከረ መልኩ እየተካሄደ መሆኑ የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ። 110 ሺህ ሔክታር መሬት በማልማት 915 ሺህ አርሶ አደሮች ከድርቅ ጉዳት መከላከል የሚያስችል የውሃ አማራጭ ለመያዝ እየተሰራ ነው ተብሏል ። በቢሮው የተፋሰስ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደስታ ገብረስላሴ ለኢዜአ ዛሬ እንደገለፁት በተያዘው የመኸር ወቅት በኤሊኖ የአየር መዛባት ምክንያት በክልሉ በሓምሌ ወር የዝናብ መቆራረጥና የእርጥበት እጥረት በስፋት ተከስቷል። በትግራይ ክልል ለድርቅ አደጋ እንዳይጋለጡ ከተሰጉ አካባቢዎችም መካከል በስፋት ምስራቃዊ፣ ደቡባዊ ምስራቅና ደቡባዊ ዞኖች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል ። በተጠቀሱ ዞኖች ውስጥ በ18 ወረዳዎች ስር የሚገኙ 124 ገጠር ቀበሌዎች በሃምሌ ወር የዝናብ እጥረትና መቆራረጥ እንዳጋጠማቸው በባለሙያዎች በተካሄደው ጥናት ተረጋግጧል ። ጣቢያዎቹ በነሃሴ ወር የተሰተካከለ የዝናብ ስርጭት እያገኙ መሆናቸውን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ ዘግይቶ መጣል የጀመረው የክረምት ዝናብ ቶሎ ሊወጣ ስለሚችል የተቀናጀ የውሃ ማቆር ስራ እየተካሄደ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ። እስከ አሁን ድረስም  ለድርቅ አደጋ ይገለጣሉ ተብለው በተሰጉ ወረዳዎች ከ90 ሺህ ኪሎሜትር በላይ ርዝመት ያለው የውሃ መውረጃ ቦይ ቁፋሮና ግንባታ ተከናውኗል ብለዋል። በተሰራው ቦይም እያንዳንዷ የውሃ ጠብታ በጎርፍ መልክ ወደ ማሳ እየገባ እንደሆነ ገልዋል። እያንዳንዳቸው 60 ሺህ ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያላቸው 81 ኩሬዎችን ተቆፍረዋል ። ከተሰሩ የውሃ ማሰባሰቢያ ኩሬዎች መካከል 26ቱ በክልሉ ባለሃብቶች ገንዘብና ዘመናዊ የማሽነሪዎች ድጋፍ የተሰሩ ናቸው። በተመሳሳይ በማሳዎች ዙሪያ ውሃ ማቆር የሚያስችሉና ከ400 ሺህ የሚበልጡ የተለያዩ የእርከን ስራዎችን እንደተዘጋጁ አቶ ደስታ ተናግረዋል ። በሃምሌና ነሃሴ ወራት የተከናወኑ የተለያዩ እርከኖች፤ኩሬዎች፤ ቦዮችና ሌሎች ስራዎች 110 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም እንዳለቸውም ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት። በእነዚህ የውሃ ማቆር ስራዎችም በክልሉ የሚገኙ ከ915 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ሊደርስባቸው ከሚችለው የድርቅ አደጋ ስራ መታደግ እንደሚቻል አመልክተዋል። የድርቅ አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶች ስኬታማ በማድረግ ራያ አለማጣ፤ራያአዘቦ እና አፅቢ ወንበርታ ወረዳዎች ግንባር ቀደም መሆናቸውን ገልጸዋል። በኤሊኖ ምክንያት የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ስጋት ለመከላክል ባለሃብቶች እና ምግባረሰናይ ድርጅቶች የሚቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ከአርሶ አደሩና መንግስታቸው ጎን እንዲቆሙም ጥሪ አስተላልፈዋል። አርሶ አደሩም ውሃ የማቆር ስራውን ከማካሄድ ጎን ለጎን ለሰውና ለእንስሳት ምግብነት ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችና የመኖ ዝርያዎችን  ማልማት እንደሚገባው አሳስቧል። በፍጥነት የሚደርሱ እንደ ገብስ፣ ሽምብራ፣ ጓያና ደቆቆ የተባለ የአተር ዝርያ መዝራት አዋጪ መሆኑን አቶ ታደሰ መክረዋል ። በትግራይ ደቡባዊ ዞን በራያ ዓዘቦ ወረዳ የፅግዓ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ግርማይ ተስፋይ በሰጡት አስተያት  እርከን በመስራት በጎርፍ መልክ የሚሄደውን ውሃ ወደ ማሳቸው በማስገባት አርጥበት ለመያዝ እየተጉ መሆናቸው ተናግረዋል። በምስራቃዊ ዞን አፅቢ ወንበርታ ወረዳ የሐየሎም ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ብርሃነ ተልደመድህን በበኩላቸው በአካባቢያቸው ዝናብ መጣል የጀመረው በነሃሴ ወር መጀመሪያ ላይ መሆኑን ተናግረዋል። ዘግይቶ የጀመረው ዝናብ ቀድሞ እንዳያቋርጥ በጎርፍ የሚወርደውን ውሃ በመጥለፍ ወደ ማሳቸው በማስገባት ቶሎ የሚደርሱ የሰብል ዝርያዎች መዝራታቸው ገልፀዋል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም