የጋምቤላ ክልል አመራር ሙስናናነ ብልሹ አሰራሮችን በመታገል ለልማት መሥራት ይጠበቅበታል-ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ

55
ጋምቤላ ነሐሴ 11/ 2011 የጋምቤላ ክልል አመራር ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በመታገል የሕዝብና የመንግሥት ሀብትን ለልማት ለማዋል መስራት እንደሚገባው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስገነዘቡ። ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሀብታቸውን ለክልሉ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስመዝግበዋል ። ርዕሰ መስተዳድሩ  በዚሁ ጊዜ እንዳሳሰቡት የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆነ ያለውን ሙስናና ብልሹ አስራርን በመታገል ለክልሉ ልማት መፋጠን የአመራር አካላት ሊንቀሳቀሱ ይገባል። ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ሀብት የማሳወቁ ተግባር አንዱ ቁልፍ መሣሪያ በመሆኑ በየደረጃው የሚገኘው አመራር ሀብቱን በማሳወቅ ኃላፊነቱ እንዲወጣ አስገንዝበዋል። በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተጀመረው የሀብትና ንብረት የማስመዝገብ ተግባርም ሌሎች አመራሮች በአርአያነት እንዲከተሉት ጠይቀዋል። የክልሉ ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ አቶ ላክደር ላክባክ በበኩላቸው ለብክነት እየተዳረገ ያለውን የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ከጥፋት ለማዳን ሀብት ምዝገባው እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። በመሆኑም ሁሉም የሕዝብ ተወካዮችና የአስፈፃሚ አካላት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ አሳስበዋል። የክልሉ ሥነ- ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሳይመን ቶሪያል በክልሉ አመራሮች የተጀመረው ሀብት የማስመዝገብ ሥራ እስከ ወረዳ ደረጃ  ባለው አደረጃጀት ለማስቀጠል  አሰራር መዘርጋቱን  ተናግረዋል። ለሥራው ስኬታማነት የሁሉንም አካላት ትብብርና ድጋፍ ጠይቀዋል። በኢትዮጵያ የባለሥልጣናት ሀብት ምዝገባ ዓዋጅ የወጣው በ2003 ነበር።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም