አትሌት ሳሙኤል ተፈራ በቤት ውስጥ ውድድር በ14 ሴኮንድ አሻሽሎ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ሆኗል

149
ነሀሴ 11/2011  በ1 ሺህ 500 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር አሸናፊ የሆነው ኢትዮጵያዊዩ አትሌት ሳሙኤል ተፈራ የዓለም ክብረ ወሰን በመሆን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ተመዘገበ። የ19 ዓመቱ አትሌት ሳሙኤል ተፈራ የካቲት 9 ቀን 2011 ዓ.ም በእንግሊዝ በርሚንግሃም ከተማ በተካሄደ የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድር የ1 ሺህ 500 ሜትር ውድድር 3 ደቂቃ ከ31 ሴኮንድ ከ4 ማይክሮ ሴኮንድ ማሸነፉ የሚታወስ ነው። አትሌት ሳሙኤል ውድድሩን ሲያሸንፍ የገባበት ጊዜም በርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰንን እንዲጨብጥ ያደረገው ነበር። የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር አሰራር መሰረት ውድድሩ የማህበሩን ዓለም አቀፍ የውድድር ደረጃ ያሟላ መሆኑን፣ የውድድር ሜዳው ደረጃውን የጠበቀ መሆኑንና የአበረታች ቅመም ምርመራ ውጤትን ሲያጣራ ቆይቷል። ማህበሩ ባደረገው ማጣራት የአትሌት ሳሙኤል ተፈራ የገባበት ጊዜ የ1 ሺህ 500 ሜትር የቤት ውስጥ የዓለም ክብረ ወሰን ሆኖ መዝግቦታል። በዚሁ መሰረት አትሌት ሳሙኤል ተፈራ የ1 ሺህ 500 ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤትነትን ከቀድሞው የሞሮኮ አትሌት ሂሻም ኤልግሩዥ ተረክቧል። ኤልግሩዥ የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የነበረው እ.አ.አ በ1997 በጀርመን ስቱትጋርት በተካሄደው የቤት ውስጥ ውድድር በ3 ደቂቃ ከ31 ሴኮንድ ከ18 ሴኮንድ በማሸነፍ ነበር። ለ22 ዓመት ሳይደፈር የቆየውን ክብረ ወሰን አትሌት ሳሙኤል ተፈራ በ14 ሴኮንድ በማሻሻል የርቀቱን የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት መሆን ችሏል። "የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት መሆኔን ሳውቅ ማመን አልቻልኩም በአትሌቲክስ ማህበሩ ውሳኔ ተደስቻለሁ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት መሆን ልዩ ስሜት የሚሰጥ ነው" ሲል አትሌት ሳሙኤል ገልጿል። በአጭር ጊዜ ባስመዘገባቸው ውጤቶች በመካከለኛ ርቀት ውድድር ውጤታማ ከሆኑ አትሌቶች ተርታ መሰለፍ የቻለው አትሌት ሳሙኤል በውድድር ቆይታው ስኬታማ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። ባለፈው ዓመት በእንግሊዝ በርሚንግሃም በተካሄደው 17ኛው ዓለም አቀፍ የቤት ወስጥ አትሌቲክስ ውድድር በ1 ሺህ 500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘበት ውጤት በዋንኛነት ይጠቀሳል። በ2019 የዳይመንድ ሊግ ውድድር ሰኔ ወር 2011 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ሉዛን ሲካሄድ በ1 ሺህ 500 3 ደቂቃ ከ31 ሴኮንድ ከ39 ሴኮንድ በመግባት በርቀቱ የግሉን የዓመቱን ምርጥ ሰአትም ማስመዝገብ ችሏል። በተመሳሳይ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ የሆነችው የአትሌት ሲፋን ሀሰን የ1 ማይል (1 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር) የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤትነትን አጽድቋል። አትሌት ሲፋን በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም በፈረንሳይ ሞናኮ ከተማ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር የ1 ማይል ሩጫ 4 ደቂቃ ከ12 ሴኮንድ ከ33 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት የርቀቱን ክብረ ወሰን ማሻሻሏ አይዘነጋም። የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር እንደ አትሌት ሳሙኤል ተፈራ ሁሉ አስፈላጊውን ማጣራት አደርጎ አትሌት ሲፋን ሀሰን የገባችበትን ጊዜ የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን አድርጎታል። ከዚህ በፊት ክብረ ወሰኑ ተይዞ የነበረው በሩሲያዊቷ አትሌት ስቬትላና ማስተርኮቫ ሲሆን እ.አ.አ በ1996 በስዊዘርላንድ ዙሪክ ከተማ በተካሄደ ውድድር 4 ደቂቃ ከ12 ሴኮንድ ከ56 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት የርቀቱ ክብረ ወሰን ባለቤት መሆኗ ይታወሳል። ለ23 ዓመት ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን አትሌት ሲፋን ሀሰን በ26 ሴኮንድ አሻሽላለች። በተያያዘ ዜና የ2019 የ11ኛ ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነገ በእንግሊዝ በርሚንግሃም ከተማ የሚካሄድ ሲሆን በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች የ1 ሺህ 500 ሜትር የቤት ውስጥ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት አትሌት ሳሙኤል ተፈራ ይሳተፋል። አትሌት ሳሙኤል እስካሁን በ2019 በ1 ሺህ 500 ሜትር በተካሄዱ ውድድሮች ስምንት ነጥብ ሰብስቦ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ኬንያዊው አትሌት ቲሞቲ ቼርዮት 31 ነጥብ ሰብስቦ በርቀቱ የዳይመንድ ሊግ ደረጃ የመጀመሪያውን ደረጃ ይዟል። አትሌት ሳሙኤል ተፈራ ከኬንያውያኑ አትሌቶች ኮርነሊስ ቱዌይና ኮርነሊስ ኪፕላንጋት ጠንካራ ፉክክር ይገጥመዋል ተብሎ ይጠበቃል። የነገው ውድድር የዳይመንድ ሊግ ነጥብ አያሰጥም። ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ጀምሮ የአትሌቲክስ ውድድሮችን ብቻ የሚካሄድበትና 12 ሺህ 700 ተመልካች በሚይዘው አሌክሳንደር ስታዲየም የዳይመንድ ሊግ ነጥብ የሚያሰጡ የአትሌቲስ ውድድሮች እና የሜዳ ተግባራት ይከናወናሉ። የ2019 የ12ኛ ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነሐሴ 18 ቀን 2011 ዓ.ም በፈረንሳይ ርዕሰ መዲና ፓሪስ የሚካሄድ ይሆናል። በእስያ፣ አፍሪካ፣ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ አህጉራት በሚገኙ 14 ከተሞች የሚካሄደው የዳይመንድ ሊግ ጳጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም በቤልጂየም ብራስልስ ፍጻሜውን ያገኛል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም