ለትውልድ ውድቀትና ጥፋትን ማውረስ አይገባም – ፕሬዚዳንት ኡሁሩ

294

ነሐሴ 11/2011 የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጳጉሜን 2 እና 3 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚካሄደው የሠላም ፌስቲቫል ላይ እንደሚገኙ አስታወቁ።

ፕሬዚዳንቱ ይህን ያስታወቁት ከአገር አቀፍ የአንድነት፣ ይቅርታና ሠላም ኮሚቴ የበላይ  ጠባቂ የቀድሞው ፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና ከኮሚቴው አባላት ጋር ባካሄዱት ውይይት ነው።

ኡሁሩ ‘ኢትዮጵያዊያን በምንም ሁኔታ ውስጥ ሆነው የማይለወጡና ለድርድር የማይቀርቡ የኬንያዊያን ወዳጆች ናቸው’ ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከቅድመ ነጻነት ጊዜ ጀምሮ የኬንያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ እንደሆነች አስታውሰው ጳጉሜን 2 እና 3 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው አገር አቀፍ የአንድነት፣ ይቅርታና የሠላም ፌስቲቫል ‘እንደራሳችሁ እንደ ኢትዮጵያዊያን ሆኜ ነው የምገኘው’ ብለዋል።

መሪዎች ለሕዝቦቻቸው ሠላምና ብልፅግናን እንጂ ውድቀትና ጥፋትን ማውረስ አይገባም ሲሉም ተደምጠዋል።

የአገር አቀፍ የአንድነት፣ ይቅርታና ሠላም ፌስቲቫሉን ያዘጋጀውና በበጎ ፈቃድ የተቋቋመው ኮሚቴ አባላት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ በፌስቲቫሉ እንዲታደሙ ከጋበዙ በኋላ ከኬንያ ግጭትን የማስወገድ ተሞክሮን እንዲያጋሩ እንደሚፈልግ ገልፀዋል።

የቀድሞው የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራኢላ ኦዲንጋም በፌስቲቫሉ ላይ እንዲሳተፉ የቀረበላቸውን ግብዣ  ተቀብለው በዝግጅቱ እንደሚገኙ ቃል ገብተዋል።

አገር አቀፍ የአንድነት፣ ይቅርታና ሠላም ኮሚቴ ሠላሟና ልማቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚል ዓላማ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከስነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ ከወጣቶችና ከሲቪል ማኅበረሰብ አባላት የተዋቀረ ኮሚቴ ነው።