በአምባሰል ወረዳ በተፈጠረ አለመግባባት የሰዎች ህይወት አለፈ

75
ደሴ ኢዜአ ነሐሴ 10/2011 ፡- በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ከቦታ ይገባኛል ጋር በተያያዘ በተፈጠረ አለመግባባት የሦስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አስታወቁ። ዋና አስተዳደሪው አቶ እሸቱ የሱፍ ለኢዜአ እንደገለጹት ችግሩ የተፈጠረው ትላንት ከሰዓት በኋላ በአምባሰል ወረዳ ዋና ከተማ ውጫሌ ውስጥ ነው። ችግሩ የተከሰተው የመኖሪያ ቦታ ለማግኘት በማህበር የተደራጁ ግለሰቦች በከተማው ቀበሌ ሁለት የቦታ ርክክብ በሚደረግበት ወቅት የአካባቢዉ ወጣቶች ቦታው ለኳስ መጫዋቻ መሆን አለበት በሚል ከባለሙያዎችና የጸጥታ አካላት ጋር በተፈጠሩት አለመግባባት እንደሆነ ተመልክቷል። ቦታው የአርሶ አደሮች የእርሻ ቦታ እንደነበረ የተናገሩት አስተዳዳሪው “አስፈላጊውን ካሳ ለአርሶ አደሮች ተሰጥቶ መግባባት ላይ ተደርሶ ነበርም “ብለዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ለወጣቶች ሌላ የኳስ መጫዋቻ ቦታ ቢሰጥም በቦታው ላይ እኛ ቤት እንስራበታለን በሚል ሌላ ችግር መፍጠራቸውን አስረድተዋል፡፡ መሬት ለመሸንሸን የሄዱ የወረዳው  ባለሙያዎችን ለማገት ሲሞክሩ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ ህይወታቸው ካለፈው ሌላ በሰባት ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት መድረሱን አቶ እሸቱ አስታውቀዋል፡፡ “ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦችም በውጫሌ ከተማ ጤና ጣቢያና በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው  ነው” ብለዋል፡፡ እንደ አስተዳደሪው ገለጻ ችግር ፈጣሪዎቹ መለየታቸውና በቁጥጥር ስር ለማዋል ዝግጅት ተጠናቋል። የከተማው ሰላም ወደነበረበት መመለሱን አመልክተው ህብረተሰቡና የጸጥታ ኃይሉ በጋራ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም