በምዕራብ ኦሞ ዞን ግጭትን ለመከላከል የሚያስችል የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው

60
ሚዛን (ኢዜአ) ነሀሴ 10 ቀን 2011- በምዕራብ ኦሞ ዞን በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰተውን ግጭትና የሰላም እጦት ለመፍታት የሚያስችል የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው። የሰላምና የጸጥታ ኮንፈረንሱ በአካባቢው ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው የሠላም ዕጦት መፍትሔ በሚያገኝበት ዙሪያ ላይ ያተኮረ መሆኑም ተመልክቷል። የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፋጅዎ ሳፒ ለኢዜአ እንደገለጹት ኮንፈረንሱ የአካባቢውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት አልሞ እየተካሄደ ሲሆን በየደረጃው ያሉ አመራሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም በመሳተፍ ላይ ናቸው። "በአካባቢው ለበርካታ ዓመታት ግጭትና አለመረጋጋት ሲፈጠር ቆይቷል" ያሉት አቶ ፋጅዎ፣ ይህም ህብረተሰቡ በስጋት እንዲኖር ከማድረጉ ባለፈ የልማት ተጠቃሚ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ነው የገለጹት። ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ ህገወጥ የመሳሪያ ዝውውርና አካባቢው ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋስን መሆኑ ለተከሰቱ ተደጋጋሚ ግጭቶች ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን አስረድተዋል። ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል የተጋነነ ጥሎሽና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ ቀጣይነት ያለው ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ እንደሚሰራም ተናግረዋል። " ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚያዋስነው ድንበር የሚስተዋለውን ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለማስቆም ከፌዴራልና ከክልል አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል። የዞኑ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ባርኮይ ወለቻንጊ በበኩላቸው እንዳሉት በአካባቢው በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው የጸጥታ ችግር ብዙ ጉዳት አድርሷል። "ከአጎራባች አካባቢዎች ጋር በመቀናጀት አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ቀጣይነት ያለው የሰላም ተግባርም ይከናወናል" ብለዋል። በኮንፈረንሱ ላይ የዞንና የተለያዩ ወረዳዎች አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የወጣቶችና የሴቶች ተወካዮች እየተሳተፉ ሲሆን ኮንፈረንሱም ለሦስት ቀናት እንደሚቆይም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም