ኤጀንሲው የግዢ ስምምነቶችን በሚጥሱ የማህበራት ኃላፊዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አድርጓል - የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ

83
አዲስ አበባ ሰኔ 6/2010 በሸማቾችና አምራቾች ማህበራት መካከል የሚደረጉ የግዢ ስምምነቶችን በማያከብሩ የማህበራት ኃላፊዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረጉን የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር እንደገለጹት፤ የአምራቾችና የሸማቾች ማህበራት ግዢ ለመፈጸም የሚያደርጉትን ስምምነት በንግድ ልውውጥ ሂደቱ ያልተገባ ጥቅም በመፈለግ የገቡትን ውል የማይጠብቁና የሚያፈርሱ በርካታ ኃላፊዎች አሉ። በዚህ የተነሳ አምራቾች በሚፈለገው ደረጃ የምርታቸው ተጠቃሚ መሆን አለመቻላቸውንና ህብረተሰቡም የአምራቾቹን  ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት አለመቻላቸውን ጠቁመዋል። ችግሩን በማስወገድ አምራቹና ሸማቹ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ በህገ ወጥ ተግባሩ ውስጥ የሚገኙትን  ለማህበራቱ አባላት በማጋለጥና ቦርዶችም እንዲያውቃቸው በማድረግ ተገቢው እርምጃ በመወሰድ ላይ ነው። እንዲህ አይነት የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ያሉባቸውን ኃላፊዎች በመገምገም በማህበራት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኤጀንሲው እርምጃ እንዲወሰድባቸው እያደረገ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል። በዚሁ መሰረት በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልል ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ከ20 በላይ ማህበራት ኃላፊዎች ከሥራ እንዲሰናበቱ መደረጉን ለአብነት አንስተዋል። በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይም ችግሩ አለባቸው በሚባሉ የማህበራት ኃላፊዎች  ላይ ግምገማ በማካሄድ እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል። ኃላፊዎቹ ላይ የተወሰደውን እርምጃ ተከትሎ በማህበራት መካከል ይስተዋል በነበረው ውል የመጣስ ተግባር ላይ ለውጦች በመምጣታቸው በቀጣይ ክትትሉ ተጠናከሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት በማህበራት መካከል የሚደረጉ የግዥ ስምምነቶችን  ያለመጠበቅ ችግርን ለመፍታት የሚያስችሉና ኃላፊዎችን በህግ ተጠያቂ የሚያደርግ ስርዓት እየተቀየሰና የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅት ከ19 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሏቸው ከ84 ሺህ በላይ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት እና 382 የህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖች በአገር አቀፍ ደረጃ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም