የመኪና መንገዱ የተሽከርካሪ ፍጥነት መቀነሻ ስላልተሰራለት ህይወታችን ለአደጋ ተጋልጧል - ነዋሪዎች

75
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 10/2011  በተለምዶ አማኑኤል ጸበል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያለው የአስፓልት መንገድ የተሽከርካሪ ፍጥነት መቀነሻ ያልተሰራለት በመሆኑ ህይወታቸው የአደጋ ስጋት ላይ መውደቁን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ለአምስት ዓመታት በግንባታ ላይ ቆይቶ ከወራት በፊት ለአገልግሎት የበቃው የአማኑኤል ፀበል የአስፓልት መንገድ ላይ የሚመላለሱ ተሽከርካሪዎች በፍጥነት የሚተላለፉ በመሆኑ ለነዋሪዎች ስጋት ሆነዋል። የአስፓልት መንገዱ ተገንብቶ ይጠናቀቅ እንጂ የተሽከርካሪ ፍጥነት መቀነሻ ያልተሰራለትና የመንገዱ ሁኔታ ለአደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ ስጋት ላይ መውደቃቸውን ነው ነዋሪዎች የሚናገሩት። ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መንገዱ ለአገልግሎት ክፈት ከመደረጉ ቀደም ብሎ በክረምት ወቅት የጎርፍ አደጋ ያጋጥማቸው እንደነበር አስታውሰዋል። የመንገዱ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ቢጀምርም የአደጋ ተጋላጭነቱ መልኩን ቀየረ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ እንዳላመጣ ተናግረዋል። በመኪና አደጋ ህይወታቸውን ያጡና ለከፋ ጉዳት የተጋለጡ የአካባቢው ነዋሪዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። በተለይም በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ስጋት እንደሆነባቸው አመልክተዋል። ነዋሪዎቹ ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ቅሬታ ብናሰማም  ምላሽ የሚሰጥ አካል አልተገኘም ብለዋል። በሰፈሩ ከ50 ዓመታት በላይ የኖሩት አቶ ገብረሚካኤል በዛ "እንደዚህ አይነት ስጋትና አደጋ ተጋርጦብኝ አያውቅም" በማለት የችግሩን ስፋት ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ታመነ በሌ እንደገለጹት፤ ህብረተሰቡን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ መንገዶችን ቅድሚያ በመስጠት እየተሰራ ነው። ነዋሪው ስጋቱን በገለጸበት በአማኑኤል ጸበል የአስፋልት መንገድ ላይ የመኪና ፍጥነት መቆጣጣሪያው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ኤጀንሲው በ2011 በጀት ዓመት ከህብረተሰቡ በተቀበለው ቅሬታ መሰረት ከዋና መንገድ ውጭ የሆኑ 60 ቦታዎች ላይ የተለያዩ የፍጥነት መቀነሻና ተያያዥ ስራዎች ማከናወኑን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም