በኢሉ አባቦርና ምእራብ ሸዋ 3ሺህ 718 ሔክታር መሬት ከተምች ነፃ ተደረገ

1704

መቱ/አምቦ ሰኔ 6/2010 በኢሉአባቦርና በምእራብ ሸዋ ዞኖች በ3 ሺህ 718 ሔክታር መሬት ላይ ተከስቶ የነበረውን የአሜሪካ መጤ ተምች በህብረተሰቡ ተሳትፎ ማጥፋት መቻሉን  የየዞኖቹ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤቶች ገለፁ ።

የኢሉአባቦር ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ለገሰ እንደገለጹት በዞኑ 11 ወረዳዎች በመስኖ እና በልግ አዝመራ በሚለማ ከ4 ሺህ 600 ሄክታር ማሳ ላይ ተምቹ ተከስቷል፡፡

አርሶአደሩ ባለፈው አመት ካገኘው ልምድ በመነሳት ማሳን በቡድን በመፈተሸ፣ በእጅ በመልቀምና በሌሎች ባህላዊ መንገዶች በመጠቀም ከ3 ሺ ሄክታር በላይ  ማሳ ከተምቹ ነፃ ማድረግ ችሏል ።

በባህላዊ መንገድ ከመከላከል በተጨማሪም ከ900 ሊትር በላይ ጸረ ተባይ መድሀኒት ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸው ተምቹን ከማሳ ላይ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት ተጨማሪ መድሀኒት ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን  አስረድተዋል፡፡

በዚህ አመት በመስኖ በለማው የበቆሎ ማሳ ላይ አስቀድሞ የታየውን ተምቹ አርሶአደሩ በቡድንና በተናጠል በመልቀም እንዳይራባ  ማድረጉን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ መስኖ ልማት ባለስልጣን ምክትል ስራ አስከያጅ አቶ በዳሳ ነጋሳ ናቸው፡፡

አርሶአደሩ ባለፈው አመት ካገኘው ልምድ በመነሳት ማሳውን በየጊዜው በመፈተሽ  ተምቹ እንዳይስፋፋ አስቀድሞ ጥረት በማድረጉ በሰብል ላይ ጉዳት ሳያስከትል መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በመቱ ወረዳ ቡሩሳ ቀበሌ አርሶአደር አለማየሁ ሽፈራው  እንዳሉት በቀን ሁለት ጊዜ ማሳቸውን በመፈተሸ ተምቹ እንዳይስፋፋ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡

”በባህላዊ መንገድ መከላከል አድካሚ ከመሆኑም በላይ ተምቹ  ቅጠል ውስጥ ስለሚደበቅ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት ከባድ ነው” ያሉት አርሶአደሩ መንግስት የጸረ ተባይ መድሀኒት በብዛት እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡

በሀሉ ወረዳ አሙማ ቀበሌ አርሶአደር  ስለሺ ኤጄርሶ  በበኩላቸው ”ተምቹን ሙሉ ለሙሉ ለመከላከል የቻልነው በባህላዊ መንገድ በእጅ በመልቀምና ማሳ በመፈተሸ ነው” ይላሉ፡፡

በልማት ቡድን አደረጃጀት ተምቹን በጋራ እንደሚለቅሙና ከአንድ ማሳ ወደ ሌላው እንዳይተላለፍ ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ 11 ወረዳዎች ከ35ሺ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እየለማ ሲሆን ከ145 ሺህ ሄክታር ደግሞ በመሀርና በልግ አዝመራ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከፅህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ   ያመለክታል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በምእራብ ሸዋ ዞን በ33 የገጠር ቀበሌዎች በ1ሺህ 577ሔክታር ማሳ ላይ ከተከሰተው ተምች  718 ሔክታሩን በባህላዊና ዘመናዊ ዘዴ ማጥፋት ተችሏል ።

በዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ፅህፈት ቤት የአዝእርት ጥበቃ ባለሙያ አቶ ደጉ ረጋሳ እንደገለጹት ተምቹን ለማጥፋት ከባህላዊ ዘዴው በተጨማሪ የኬሚካል ርጭት ተካሔዷል ።

የአምቦ ወረዳ አርሶ አደር ቶለሳ ፊጣ በሰጡት አስተያየት ተምቹ በሰብላቸው ላይ ጉዳት ሳያስከትል ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር ሆነው በእጅ በመልቀም  መከላከላቸውን ገልፀዋል፡፡

ተምቹ ዳግም እንዳይከሰትም በልማት ቡድናቸው አማካኝነት የተጠናከረ ቁጥጥር እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ከባለሙያ ባገኙት የግንዛቤ ትምህርትና ካለፈው አመት  ልምድ  በመነሳት ዘንድሮም ተምቹ በምርታቸው ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ቅድመ ጥንቃቄ እየወሰዱ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የሊበን ጃዊ ወረዳ አርሶአደር ንጉሴ አየለ ናቸው፡፡

በምእራብ ሸዋ ዞን በ2010/011 ምርት ዘመን 615 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ለማልማት የሚያስችል የእርሻ ስራ እየተካሄደ መሆኑንም ከፅህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።