ልጃገረዶች የአሸንዳ በዓልን በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ሊያግዙ ይገባል

104
መቐለ ኢዜአ ነሓሴ 10/2011 ልጃገረዶች የአሸንዳ በዓልን ጥንታዊ ይዘቱን ሳይለቅና ሳይበረዝ በዓለም ቅርስነት ለመመዝገብ የተጀመረውን ጥረት ሊያግዙ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ጠየቁ ። ልጃገረዶች የአሸንዳ በዓልን  ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ በአለም ቅርስነት እንዲመዘገብ በሚያስችል መልኩ ሊያከብሩት ይገባል ብለዋል ። በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በየዓመቱ ከነሃሴ 16 ጀምሮ በልጃገረዶችና በወጣት ሴቶች ዘንድ በድምቀት ይከበራል። የአሸንዳ በዓል አስመልክተው ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች እንዳሉት በዓሉ ሳይበረዝና ሳይከለስ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተጠብቆ መተላለፍ አለበት። የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ቄስ አረጋዊ ፀጋይ እንዳሉት ከጥንት ጀምሮ በየዓመቱ በልጃገረዶች ዘንድ የሚከበረውን የአሽንዳ በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ይዘቱ ተጠብቆ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል ። የበዓሉ ዋና ባለቤቶች የሆኑ ልጃገረዶችና ሴቶች በዓሉን በባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች ደምቀውና ተውበው ማክበር አለባቸው። በበዓሉ ወቅት የአሸንዳ ልጆች  ውሎአቸው ሰላማዊና ቀና እንዲሆን ማድረግ ለባህላቸው ያላቸውን ፅናትና ክብር የሚያሳዩበት በዓል ነው ብለዋል። የበዓሉ ባለቤቶች አሸንዳ  ጥንታዊ ይዘቱን ሳይለቅና ሳይበረዝ በዓለም ቅርስነት ለመመዝገብ የተጀመረውን ጥረት ሊያግዙ ይገባል ብለዋል።” የአሸንዳ በዓል ተሳታፊ ልጃገረዶች በዓሉን ለቱሪስቶች መስህብነት እንዲውል፣የሃገራችን ልዩ መገለጫ እንዲሆንና ክብሩን ጠብቆ እንዲቀጥል ልጃገረዶች የወላጆቻቸው አርአያ መከተል አለባቸው” ያሉት ደግሞ የመቀሌ ከተማ የሃገር ሽማግሌ አቶ በየነ ይልማ ናቸው። ይህ ባህል እያደገ እንዲሄድና የቱሪስት መስህብነቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ህብረተሰቡ በእኔነት መንፈስና በባለቤትነት ልጆቹ ባህላዊ አልባሳት አጊጠው በዓሉን እንዲያከብሩ ማነሳሳት አለበት ብለዋል። በመቀሌ የዓዲ ሓቂ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አወጣሽ ታደለ በበኩላቸው በኛ ጊዜ አሸንዳ ለመጫወት ከሳምንት በፊት የራሳችንን ባህላዊ ጌጣጌጥ አዘጋጅተን ከሌለን ደግሞ የእናቶቻቸን ተውሰን ጥንታዊ ባህሉን ጠብቀን እናከብረው ነበር ብለዋል። በዘንደሮው የአሸንዳ በዓል ላይ የሚሰተፉ ሁለት ሴት ልጆቻቸውን ባህሉን ሳይበረዝና ሳይከለስ እንዲያከብሩት ባህላዊ አልቦ፤የአገር ባህል ልብስ፤የእጅ አምባርና ሌሎች ጌጣጌጦችን እንደገዙላቸው ተናግረዋል። የ17 ዓመት ታዳጊ ወጣት የሆነችው አለም ግርማይ እንዳለችውም፣በበዓሉ ላይ ደምቃ ለመታየትና ለመጫወት የተጠለፈ አቡጀዲድ ቀሚስና ነጠላ፤ የአንገትና የጆሮ ጌጣጌጦች መግዛቷን ተናግራለች። ሶስት ሴት ልጆቻቸውን ይዘው በበዓሉ ላይ ለመታደም ከአዳማ ወደ መቀሌ ከተማ መምጣታቸውን የተናገሩት አቶ ዕቁባይ በርሀ በበዓሉ ላይ መታደም በየዓመቱ የሚከውኑት ተግባር መሆኑን ገልፀዋል ። ” በዓሉ ሁሌም በናፍቆትና በፍቅር የሚጠበቅ ነው” ያሉት አቶ ዕቁባይ ልጃገረዶች በዓሉን ይዘቱን ጠብቀው እንዲያከብሩትና እንዲጠብቁት ምክራቸውን ሰንዝረዋል  ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም