"ዛሬ የምንወጣው የዜግነት አገልግሎት የመጪውን ትወልድ ዕጣ ፈንታ ይወስናል"- የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

88

ኢዜአ፤ ነሐሴ 10/2011 "ዛሬ የምንወጣው የዜግነት አገልግሎት የመጪውን ትወልድ ዕጣ ፈንታ ይወስናል " ሲል የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ  መንግስት ገለጸ።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ  መንግስት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

የኦሮሚያ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በላከው የአቋም መግለጫ የኦሮሞ ህዝብ ዛሬ የነጻነት ጸሐይ የታየባትን ኦሮሚያን እውን ለማድረግ በርካታ መስዋዕትነትን መክፈሉን አስተውሶ፤በተከፈለው መስዋዕትነትም የነጻነት አየር የሚተነፍስባትን የዛሬዋን ኦሮሚያን ማየት መቻሉን ጠቅሷል።

የኦሮሞ ህዝብ የመጣበት መንገድ ዛሬ የደረሰው ደረጃ ላይ ብቻ ሊደርስ አለመሆኑና ያለውን አኩሪ ባህልና ወግ ተጠቅሞ ሀገርን በመገንባት ለመጪው ትውልድ ለማስተላላፈ ዓላማ ያደረገ እንደሆነም ተገልጿል።

ረጅም ዓመት የወሰደው ትግልም በርካታ መስዋዕትነትን ያሥከፈለ ቢሆንም በአንድ በኩል ኦሮሚያን በሌላ በኩል ደግሞ ሀገርን ከዘራፊዎች ነጻ በማድረግ፣ ነጻነት እና እኩልነት እንዲመጣ ማድረጉን የጠቀሰው መግለጫው፤ ለውጥ የመጣበት መንገድ ዘላቂ እንዲሆን በአንድነትና በመደማማጥ መቀጠል አለበት ብሏል።

“የኦሮሞ ህዝብ ለጥቃት እጅ አልሰጥም በማለት እራሱ ታግሎ ሌሎችም እንዲታገሉ አድረጓል፤  አይቻልም የተባለው እንዲቻል አድርጎም ለሰፊው የሀገሪቱ ህዝቦች አሳይቷል፤ ለሀገሪቷ ተስፋ በመሆን ሌሎችን ከጭለማ ውስጥ አውጥቷል፤ ይህ ረጅም መንገድ የወሰደው ትግልም ዛሬ የምናያትን የበለጸገች ኦሮሚያን ለመገንባት መሰረት ሆኗል’’ ሲልም መግለጫው ይጠቅሳል።

አሁን የተደረሰበት የትግል ምዕራፍም ወደ ሌላኛው ተሸጋግሮ ዋነኛ የሀገሪቷ ጠላት የሆነውን ደህነትን በመታገል፤ በኦሮሚያ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ነገ ወደሚፈልገው ምዕራፍ ለመሸጋገር ሁሉም የዜግነት ድርሻውን በተገቢው መንገድ ሊወጣ እንደሚገባም ተገልጿል።

የዜግነት አገልግሎት አዋጅ በጨፌ ኦሮሚያ ጸድቆ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ባህሉንና ወጉን ጠብቆ የሚጠበቅበትን የዜግነት አገልግሎት እንዲወጣ ወደ ተግባር ከተገባ ወዲህም በክልሉ አኩሪ የሚባሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ነው መግለጫው የጠቀሰው።

የዜግነት አገልግሎቱን ዓላማ በመረዳት ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ቆርጦ ለተነሳውን ህዝብ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ታላቅ አክብሮት አለው ብሏል።

በክልሉ በገዳ ስርዓት ባህል ማንኛውንም ችግር በመፍታት፣ ችግሮች ሲፈጠሩም በውይይት ብቻ እንዲቋጩ በማድረግ አሁን የተገኘው ሰላም እውን እንዲሆን  አስችሏል ያለው መግለጫው፤ የገዳ ስርዓት ችግኝ መትከልና መንከባከብን ስላስተማረን በአንድ ቀን 211 ነጥብ 9 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ታሪክ እንድንሰራ ማድረጉም ተጠቅሷል።

ኦሮሞነት መተጋገዝ፣ መዋደድ፣ ችግርን በጋራ መፍታት  በመሆኑ አሁን የተጀመረው የዜግነት አገልግሎትም በዚሁ መንፈስ እውን ሊሆን እንደሚገባም የጠቆመው መግለጫው፤ ለማሳያነትም በክልሉ በአንድ ዞን ብቻ የተለገሰ ደም የበርካቶችን ህይወት የሚታደግ መሆኑና ለሌሎችም አርዓያ እንደሆነ ተጠቅሷል።

በክልሉ የበርካታ የአቅመ ደካሞች ቤት በማደስ፤ የመማሪያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረግ  አቅመደካማ እናቶች ደስ እንዲሰኙና ወጣቱም የተገኘውን ነጻነት ተጠቅሞ እንዲማር ያግዘዋል ነው የተባለው።

በሌላ በኩል በርካቶች የአከባቢያቸውን ጽዳት በመጠበቅና በዘመቻ በማጽዳት ለመኖር ምቹ የሆነን አካባቢ በመፍጠር ላይ እንደሆነ የጠቀሰው መግለጫው፤ በመጪው እሁድ በሚካሄደው ብሔራዊ የጽዳት ዘመቻ የሚደምቅ ይሆናል ተብሏል።

በክልሉ እየተሰጠ የሚገኘው የዜግነት አገልግሎት በአንድ ጀምበር ብቻ አውን የሚሆን ባለመሆኑ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል በተጠናከረ መልኩ ይሰራል ነው የተባለው።

ያልተማረ፣ ያልተደራጀና ድህነት ማነቆ የሆነበት ህዝብ መቼም ቢሆን አያሸንፍም ያለው መግለጫው፤ ለዚህም በተደራጀ መንገድ የዜግነት አገልግሎት በመስጠት ለበለጠ ድል ራሳችንን ማዘጋጀት ይጠበቅብናል ነው ያለው።

የኦሮሞ ህዝብ አሁን እንደጀመረው ሁሉ ሰላሙን በማስጠበቅ፣ በልማት ለመሳተፍና ዴሞክራሲን ለመገንባት በተደራጀ መልኩ መንቀሳቀስ ይኖርበታል ነው ያለው መግለጫው።

አሁን የተገኘውን ድል ወደ ኋላ ለመመለስ በርካቶች እያሤሩ ነው ያለው መግለጫው፤ “ሴራቸው እነሱን ወደ መቃብር ከማውረድ ውጪ” የተጀመረውን ለውጥ ለሰከንድም ወደ ኋላ ሊመልሰው እንደማይችልም ጠቅሷል።

በዚህም ህዝቡ፣ ቄሮና ቀሬዎች እንዲሁም ምሁራኖች የተሳተፉበት የዜግነት አገልግሎት በመስጠት የህዝባችንን የወደ ፊት ህይወት የለመለመ ማድረግ ይጠበቅብናል ነው ያለው።

የክልሉ ኢኮኖሚ እንዲያድግ ግብርን መሰብሰብ፣ ህገ ወጦችንና አድርባዮችን በማጋለጥ የዜግነት ግዴታችንን እንወጣ ያለው መግለጫው፤ የዜግነት አገልግሎት ትውልድን የሚያስተምር፣ የውድድር መንፈስን የሚፈጥር፣ የስራ ባህልን የሚያሻሽልና ድህነትን ለማሸነፍ የሚረዳ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ የክልሉ መንግስት ባወጣው የአቋም መግለጫ መልዕክት አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም