የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ዘላቂነት ለማረጋገጥ ቆሻሻው ለፕሮጀክቱ በሚስማማ መልኩ መዘጋጀት አለበት

112
ነሐሴ 10/2011 የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ዘላቂነት ለማረጋገጥ ቆሻሻው ለፕሮጀክቱ በሚስማማ መልኩ መዘጋጀት እንዳለበት ተገለጸ። የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላትና የክፍለ ከተማ ደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች የፕሮጀክቱን አተገባበርና እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን በመለየት የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ የማስቻል ዓላማ ያለው ጉብኝት አካሂደዋል። ሃይል ማመንጫው ከከተማው የሚሰበሰበውን ቆሻሻ በአምስት መድፊያ በሮች በማከማቸትና የተለያዩ ደረጃዎችን በማለፍ እስከ 25 ሜጋ ዋት ድረስ ኃይል እያመነጨ ይገኛል። የአዲስ አበባ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ ለማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ በየቀኑ ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚሆነውን ደረቅ ቆሻሻ እያስወገደ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። ፕሮጀክቱ አስተዋጽኦ እያደረገ ቢሆንም ዘላቂነቱን የሚፈታተን የቆሻሻ አቅርቦት ችግር እየተስተዋለ እንደሆነ አቶ እሸቱ ጠቁመዋል። ድንጋይ፣ ትልልቅ ብረቶች፣ ግንድና ጭቃን የመሳሰሉ ቆሻሻዎች ተደባልቀው እየመጡ ችግር እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም የፕሮጀክቱን ህልውና ለማስቀጠል ለሃይል ማመንጫ የሚጠቅም ቆሻሻ በአግባቡ ተለይቶ ስራ ላይ መዋል እንዳለበት አስገንዝበዋል። ጽዳት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንደሆነ የተናገሩት አቶ እሸቱ፤ የመዲናዋ ነዋሪዎች የሚጥሉትን ቆሻሻ በአግባቡ በመለየት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። ከክፍለ ከተማ የመጡ የደረቅ ቆሻሻ ጽህፈት ቤቶች በዚህ በኩል የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትና ቆሻሻዎች ተለይተው እንዲቀርቡ የተጠናከረ ተግባር ሊያከናውኑ እንደሚገባም አሳስበዋል። ''ቆሻሻ የሚያነሱ ማህበራት ብር ብቻ ማየት የለባቸውም'' የሚል ሀሳብ ያንጸባረቁት ሥራ አስኪያጁ፤ ''ፕሮጀክቱ ትልቅ የአገር ኃብት በመሆኑ እንዳይበላሽ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይከናወናል'' ብለዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሪት ሰብለወንጌል አዱኛ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የመዲናዋን ቆሻሻ ከማስወገድ ባለፈ በኃይል ልማት ዘርፍ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አድንቀዋል። እንዲያም ሆኖ ተረፈ ምርት አወጋገድ ላይ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ''በተለይ ከምርት በኋላ የሚወገደው አመድ በአግባቡ ካልተወገደ የጤና ጠንቅ ሊሆን የሚችል ነው'' ሲሉ ምልከታቸውን ገልጸዋል ። በመሆኑም ምክር ቤቱ የተረፈ ምርት ማስወገጃ መሳሪያዎችን እጥረት ለማቃለል በተለይ የመኪና አቅርቦትን ለማሟላት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። የፕሮጀክቱ ሌላው ጉዳይ የሰው ኃይል እጥረት መሆኑን ያመለከቱት ሰብሳቢዋ ችግሩን ለመፍታት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል። የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት በ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ወጪ ተገንብቶ ነሐሴ 13 ቀን 2010 ዓ.ም ቢመረቀቅም  ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ከገባ ግን  አራት ወራት ተቆጥረዋል። ከአምስት አመት በፊት በ2006 ዓ ም ግንባታው የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በተመረረቀበት ወቅት በአመት በአማካይ 185 ጊጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ ተገልጾ ነበር፡፡ ኃይል ለማመንጨት በቀን 1 ሺህ 400 ቶን ደረቅ ቆሻሻ በግብዓትነት ይጠቀማል፡፡ የፕሮጀክቱ ሙሉ ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ነው፡፡ ስራውን ያከናወነው ካምብሪጅ ኢንዱስትሪ ሃላፊነቱ የተወሰነ ሲሆን በንዑስ ተቋራጭነት የቻይናው ኤሌክትሪክ ኢንጂነሪንግ ሊሚትድ (CNEEC) ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም