''ደስተኛ ህጻናት ለአዲስ አበባ '' በሚል የህጻናት ስፖርት እንቅስቃሴ ሊካሄድ ነው

65
ነሐሴ 10/2011 ''ደስተኛ ህጻናት ለአዲስ አበባ '' በሚል መሪ ቃል ብዙሃን የሚሳተፉበት የስፖርት እንቅስቃሴ በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ መሰቀል አደባይ እንደሚካሄድ ተገለጸ። በዝግጅቱ በህጻናት የሚወደዱት ኤልሞና ኢትዮጲስ እንዲሁም ታዋቂ አርቲስቶ የሚገኙ ሲሆን ለህጻናት የሚቀርቡ የተለያዩ ፕሮግራሞች የዝግጅቱ አካል መሆናቸው ነው የተነገረው። የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ አብርሃ ዓላማው ጠንካራ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ እርስ በእስር ጥሩ ግንኙት ያላቸውንና አገር ተረካቢ የሚሆኑ መልካም ዜጎችን ማፍራት እንደሆነ ነው የገለጹት። በዝግጅቱ ህጻናት የአገራቸውን ባህል እንዲያውቁ የሚያስችሉ የተለያዩ የባህል ስፖርቶችና ጨዋታዎች የሚያካሂዱበት ነውም ተብሏል። በዝግጅቱ ከሁለት እስከ 12 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ህጻናት ይካፈላሉ። የብዙሃን የስፖርት እንቅስቃሴው ሲዘጋጅ የመጀመሪያ ይሁን እንጂ በቀጣይ በየሳምንቱ በአካባቢያቸው በተመረጡ ቦታዎች መሰል ዝግጅት ይካሄዳል ተብሏል። በየስድስት ወሩ ደግሞ ሁሉንም በጋራ የሚያገናኝ ፕሮግራም በአዲስ አበባ መመስቀል አደባባይ ይካሄዳል። ስፖርታዊ እንቅስቃሴው በሚካሄድበት አካባቢ መንገዶች ከተሽከርካሪ ነጻ እንደሆኑና ዝግጅቱ ከጠዋቱ 1 ሰዓት ከ30 ጀምሮ እስከ 3 ሰዓት ከ30 ድረስ እንደሚቆይ ታውቋል። ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የህጻናት የብዙሃን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ላይ ከ25 ሺህ በላይ ህጻናት ይካፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል። በመዲናዋ ስፖርት ኮሚሽን እና የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ትብብር የሚዘጋጅ መሆኑም ነው የተገለጸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም