የስደተኞች ሰቆቃ በባህረ ሰላጤው ሸለቆ

115
ሰለሞን ተሰራ (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ስደት መውጣታቸው የተለመደ ተግባር ከሆነ ውሎ አድሯል። ስደት መውጣቱ ብቻ ሳይሆን የመረጡት ህገወጥ የስደት መንገድ ለከፋ አደጋ ያጋልጣቸዋል። በዚህም በርካታ ለመስማት የሚቀፍ ዜናዎችን ሰምተናል። ዜናውን ሰምተን ብቻ አላቆምንም። አሁንም የህገወጥ ስደቱና የሰቆቃ ታሪኩ እንደቀጠለ ነው። ከሰሞኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል የሚሰራው ሂውማን ራይትስ ዋች ያወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኤደን ባህረ-ሰላጤ የከፋ የስደት ጉዞ እያጋጠማቸው እንደሆነ አመልክቷል። ኢትዮጵያውያን በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ-ሰላጤ በኩል በሚያደርጉት የስደት ጉዞ የመን ሲደርሱ በተደራጁ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሰንሰለት ለብዝበዛና ለአካላዊ ጥቃት እንደሚጋለጡ 'ሂዩማን ራይትስ ዋች' ትናንት ባወጣው ሪፖርቱ አስታውቋል። በተጨማሪ ''በግዴታ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ከመደረጉ በፊት በሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ እስር ቤቶች አስከፊ ተግባር ይፈጸምባቸዋል'' ብሏል። በኢትዮጵያ፣ የመንና ሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ባለስልጣናት የስደተኞቹን ፈተና ለማቃለል፣ የመኖሪያ ፈቃድ አሰጣጥና በጸጥታ ሰራተኞች የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም የሚያደርጉት እንቅስቃሴም ደካማ መሆኑን ሪፖርቱ አመላክቷል። ባለፉት 10 አመታት በአገሪቱ የነበረው ስራ አጥነት፣ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት፣ ድርቅ እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በጀልባና በእግራቸው በየመን አቋርጠው ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል። ስደተኞቹ ሳዑዲ አረቢያንና የባህረ ሰላጤውን አገሮች የሚመርጡት የስራ እድል እናገኛለን በሚል እሳቤ መሆኑም ተገልጿል። ጉዟቸው ህገ ወጥ በመሆኑ አብዛኞቹ ወደ አገሮቹ ሲገቡ የሚጋፈጡት መከራ ለሰቆቃ እንደዳረጋቸው ይታመናል። “በሳዑዲ አረቢያ የተሻለ ህይወት እናገኛለን በማለት ተስፋ አድርገው የሚጓዙት ኢትዮጵያውያን በጉዟቸው ላይ ለመስማት የሚዘገንን ስቃይ ይደርስባቸዋል፤ ከነዚህም መካከል በባህር ውስጥ ሰምጦ መሞት፣ አካላዊ ጥቃት እና ብዝበዛ ይጠቀሳሉ” በማለት በሂዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ተመራማሪው ፌሊክስ ሆም ተናግረዋል። ”የኢትዮጵያ መንግስት ባዶ እጃቸውን ወደ አገራቸው የሚመለሱትን ስደተኞች ከአለም አቀፍ ለጋሾች ጋር በመተባበር ድጋፍ እንደሚያደርግላቸውና አሁንም ድጋፉ መቀጠሉን“ ተመራማሪው ጠቁመዋል። ሂዩማን ራይትስ ዋች ከታህሳስ 2010 እስከ ግንቦት 2011 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው 12 ኢትዮጵያውያን የጉዞውን አስከፊነት ነግረውታል። በተጨማሪ የሰብአዊ ተቋማት ሰራተኞችንና በኢትዮጵያ ከስደተኞች ጉዳይ ጋር የተያያዘ ስራ የሚሰሩ ዲፕሎማቶችን በማነጋገር ሪፖርቱ መዘጋጀቱ ተገልጿል። አለም አቀፉ የስደተኞች ማህበር እንዳስታወቀው የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ከህዳር 2009 ዓ.ም አንስቶ ስደተኞችን በግዳጅ ወደ አገራቸው መመለስ ከመጀመሩ በፊት በአገሪቱ 500 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ይኖሩ ነበር። በዚህም ከግንቦት 2009 እስከ መጋቢት 2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ 260 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በአማካይ በየወሩ 10 ሺህ ሰዎች በግዳጅ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል። አለም አቀፉ የስደተኞች ማህበር አንዳስታወቀው በግዳጅ ወደ አገራቸው የመመለሱ ሂደት አሁንም ቀጥሏል። የሳዑዲ አረቢያ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ከተለያየ ዓለም በመምጣት በሳዑዲ እየኖሩ ህግ የጣሱ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች በፖሊስ ታስረዋል። ከነዚህ መካከል 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚሆኑት የመኖሪያ ህጉን በመጣስ፣ 557 ሺህ የአሰሪና ሰራተኛ ህጉን በመጣስ፣ 237 ሺህ የሚጠጉት ደግሞ ከድንበር መጣስ ጋር የተያያዘ የህግ መተላለፍ በመፈጸም መታሰራቸውን ተገልጿል። በተጨማሪ 61 ሺህ 125 ሰዎች በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ጥሰው ወደ አገሪቱ ሲገቡ ተይዘው ታስረዋል። ከነዚህ ውስጥ 51 በመቶ የሚጠጉት ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ በአጠቃላይ 895 ሺህ የሚጠጉት ኢትዮጵያውያን ደግሞ በግዳጅ ወደ አገራቸው የሚመለሱ መሆናቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል። ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው 12 ኢትዮጵያውያን እንደገለጹት፤ ስደቱ የሚከናወነው ከኢትዮጵያ ተነስተው ጅቡቲ፣ ሶማሌላንድ፣ ፑንትላንድ፣ የመን አድርጎ ሳኡዲ አረቢያ መዝለቅን ያጠቃልላል። በተለይ የመን ላይ የከተሙ ህገወጥ አዘዋዋሪዎች የማስለቀቂያ ገንዘብ ከማስከፈላቸው ባለፈ አካላዊ ጥቃት በመፈጸም የሚታወቁ ናቸው። ህገወጥ አዘዋዋሪዎቹ በአጋሮቻቸው በኩል የስደተኞቹን ቤተሰቦች በመገናኘት፣ በማስፈራራትና አካላዊ ጥቃት በማድረስ ገንዘቡን እንደሚቀበሉ ቃለ መጠይቁን የሰጡት ግለሰቦች ለሂዩማን ራይትስ ዋች ተናግረዋል። ስደተኞቹ እንደገለጹት፤ በኤደን ሰርጥ ወይም በቀይ ባህር በኩል የመን ለመድረስ የሚደረገው ጉዞ 24 ሰዓት የሚፈጅ እንደሆነና ጉዞው ከአቅማቸው በላይ በጫኑ ጀልባዎች እንደሚደረግም ተናግረዋል። አብዛኛውን ጊዜ ጀልባዎቹ በሰዎች የተጨናነቁ ውሃና ምግብ የማይኖርበት እንዲሁም በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ሰውነትን ማንቀሳቀስ የተከለከለበት መሆኑንም ገልጸዋል። "እኔ በተሳፈርኩበት ጀልባ 180 ሰዎች ነበሩ ከነዚህ መካከል 25 ቱ በጉዞው ላይ ሞተዋል። ምክንያቱ ደግሞ የባህር ሞገዱ በማየሉና ጀልባዋ ከአቅሟ በላይ ሰዎችን በመጫንዋ መናወጥ በመጀመሯና ለመስመጥ መቃረቧን ተከትሎ ደላሎቹ 25 ሰዎችን በዘፈቀደ መርጠው ወደ ባህሩ በመጣላቸው ነው"  በማለት አንዱ ስደተኛ የጉዞውን አስከፊነት ተናግሯል። ስደተኞቹ እንደተናገሩት፤ በህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እጅ የወደቁት የመን ከገቡ በኋላ ነው። አምስቱ ስደተኞች ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ አካላዊ ጥቃት እንዳደረሱባቸውና በኢትዮጵያና ሶማሊያ በሚገኙ አጋሮቻቸው በኩል ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንደተቀበሉ ተናግረዋል። በተለይ በየመናውያን በሚተዳደሩ ካምፖች ውስጥ የተጠለሉ ኢትዮጵያውያን ከፍ ያለ አካላዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ተገልጿል። የስደተኞቹ ቤተሰቦች በአብዛኛው የተጠየቁትን የማስለቀቂያ ገንዘብ የሚከፍሉት ቤታቸውን ወይም መሬታቸውን አለፍ ሲልም ያላቸውን ንብረት በመሸጥ መሆኑን ገልጸዋል። ''ለህገወጥ አዘዋዋሪዎቹ የተጠየቁትን ገንዘብ ከከፈሉ ወይም ማምለጥ ከቻሉ ወደ ሰሜናዊው የየመንና ሳኡዲ አረቢያ ድንበር በመጠጋት ተራራማ አካባቢዎችን አቋርጠው ይጓዛሉ። በዚህ ወቅት የሳኡዲ ድንበር ጠባቂዎች ተኩስ በመክፈት ይገድሏቸዋል፣ ያቆስሏቸዋል እድል የቀናው ደግሞ ድንበሩን አልፎ ሳኡዲ አረቢያ ይገባል'' በማለት ስደተኞች ተናግረዋል። በጉዟቸው ወቅት በየመንገዱ ብዙ ሬሳ ወድቆ መመልከታቸውንም በተሰበረ ልብ ገልጸዋል። ድንበሩን አልፈው የገቡትም ቢሆኑ ብዙም ሳይቆዩ በሳኡዲ ፖሊሶች መያዛቸውንና የአገሪቱ እስር ቤቶች ሁኔታ አሰቃቂ አካላዊ ጥቃት የሚፈጸምበት፣ በቂ ምግብ የማይቀርብበት፣ የሽንት ቤትና የህክምና አገልግሎት የማይሰጥበት፣ የተጨናነቀና ድብደባ የሚፈጸምበት እንደሆነ የችግሩ ሰለባዎች እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱትን ስደተኞች አለም አቀፍ የሰብአዊ ተቋማት ቦሌ አየር ማረፊያ በመገኘትና በመለየት ድጋፍ የሚያደርጉላቸው ሲሆን አብዛኛዎቹ ግን በቀጥታ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንደሚሄዱም ተገልጿል። ከስደት ተመላሾቹን መልሶ ለመቋቋም የገንዘብ ልገሳ የሚያደርጉ ተቋማት እንዳስታወቁት፤ ወደ አገር ቤት የተመለሱት አብዛኛዎቹ ስደተኞች ምንም ገንዘብ ወይም ንብረት ሳይዙ የሚመጡ ናቸው። ስደተኞቹ አዲስ አበባ ሲገቡ የሚደረግላቸው ድጋፍ አነስተኛና የደረሰባቸውን አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ለመጠገን በቂ አለመሆኑም ተጠቅሷል። በተለይ ወደ ክልል የሚጓዙ ስደተኞች ከትራንስፖርት ያለፈ አመርቂ ድጋፍ አይደረግላቸውም። ሂዩማን ራይትስ ዋች እንዳስታወቀው፤ ስደተኞችን በተመለከተ ለአገሪቱ ድጋፍ የሚያደርጉ አለም አቀፍ ለጋሽ ተቋማት ትኩረታቸው ከአፍሪካ ቀንድ ወደ አውሮፓ የሚደረገውን ጉዞ ለመከላከልና ለተመላሾቹ ድጋፍ ለማድረግ  ሲሆን ከሳኡዲ አረቢያ ለሚመለሱ ስደተኞች የሚደረገው ድጋፍ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑንም ይጠቁሟሉ። “የሳኡዲ መንግስት በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው መመለሱን የቀጠለ ሲሆን ስደተኞቹ ከእዳና ስነ አእምሯዊ ጉዳት በስተቀር ምንም የሌላቸው ናቸው” በማለት ተመራማሪው ፌሊክስ ሆም ተናግረዋል። የሳኡዲ መንግስት ስደተኞቹ በግዛቱ በሚቆዩበት ወቅት ጥበቃ የማድረግና ከህገ ወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች የመከላከል ግዴታ አለበት፤ በአገሪቱ ወኪሎችና በወንጀለኞቹ መካከል ግጭት አለመኖሩን በማረጋገጥ የስደተኞቹን የግዳጅ እስርና ወደ አገራቸው መመለስ መታገል አለበት” በማለት የተቋሙ የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪው ፌሊክስ ሆም ያስገነዝባሉ። የባህረ ሰላጤው ስደተኞች የሰቆቃ ጉዞ መፍትሄ ይፈልጋል። ዋናው መፍትሄ ያለው ግን ስደተኞች ከሚነሱባቸው አገሮች መዳፍ ነው። አገሮቹ ዜጎቻቸው የስደት ጎዳናን ይዘው ሲነጉዱ የሚደርስባቸውን ለጆሮ የከበደ ሰቆቃ ለመከላከል ስደትን አማራጭ አድርገው እንዲሄዱ የሚገፏቸውን ምክንያቶች ማድረቅ ይጠበቅባቸዋል። በተለይም የኢኮኖሚ ችግር መፍታትና አማራጭ ማቅረብ ላይ መስራት ግድ ይላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ህጋዊ መንገድን ተከትለው የሚሄዱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ተገቢነት ይኖረዋል። በኢትዮጵያም ህገወጥ ስደትን ለማስቀረት የተጀመሩ ጥረቶችን ውጤታማ ለማድረግ መስራት ያስፈልጋል። ህግ ማውጣት፣ ተቋማት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ማድረግና ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን አደብ ማስያዝ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም