የፊቼ ጫምባላላ በዓል በሰላም መጠናቀቁን ፖሊስ አስታወቀ

3254

ሀዋሳ ሰኔ 6/2010 የሲዳማ ዘመን መለወጫ የሆነው የፊቼ ጫምባላላ በዓል በሰላም መጠናቀቁን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በበዓሉ ላይ አንዳንድ  ግለሰቦች በፈጠሩት ትንኮሳ በተነሳው ግጭት በሰውና በንብረት ላይ የጎላ ጉዳት ሳይደርስ ፖሊስ መቆጣጠሩም ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በወልቂጤ ከተማ በእግር ኳስ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና በንብረት ላይም ጉዳት መድረሱን  የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አህመድላዲን ጀማል ለኢዜአ እንደገለጹት ከትናንት ጀምሮ በሀዋሳ ሲከበር በቆየው የፊቼ ጨምባላላ በዓል ላይ ብዛት ያለው ህዝብ ተሳትፏል፡፡

ለበዓሉ የወጣውን ከፍተኛ ቁጥር ህዝብ መጠቀሚያ ለማድረግ አንዳንድ ግለሰቦች ባደረጉት ትንኮሳ ግጭት መከሰቱን  ተናግረዋል፡፡

በዚህም በሰው ላይ ቀላል የመቁሰልና የንብረት ጉዳተት መድረሱን  አመልክቷል፡፡

በዓሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር ለማድረግ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ችግሩን ፈጥኖ ለመከላከል ባደረገው ጥረት በዓሉ በሰላም ተጠናቆ ህዝቡ ወደ የመጣበት መመለሱን አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በወልቂጤ ከተማ ይጫወቱ በነበሩ እግር ኳስ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል  አለመግባባት ተፈጥሮ  ጉዳት መድረሱን  የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፈቱ ሰማን ገልጸዋል፡፡

ከትናንት በስቲያ በሁለት እግር ኳስ ቡድኖች ደጋፊዎች ተከስቶ የነበረው  ይሄው አለመግባባት ወደ ግጭት በማምራቱ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና በንብረት ላይም ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል፡፡

” ግጭቱን ለማረጋጋት የዞን፣ የክልልና የፌደራል ጸጥታ አካላት በቅንጅት እየሰሩ በመሆኑ አካባቢው እየተረጋጋ ነው” ብለዋል፡፡