በቀጣይ ዓመት ለሚተከለው ችግኝ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ ነው

62
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሃሴ 10 /2011 በክረምቱ ከነበረው የችግኝ ተከላ ትምህርት በመውሰድ በቀጣይ ዓመት ለሚካሄደው ተከላ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ። በክረምቱ ወቅት አራት ቢሊዮን ችግኝ ተከላ የሚካሄድበትን ብሔራዊ የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ግንቦት 18 ቀን 2011 ዓ.ም ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታም ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ለችግኝ ተከላው ከተቋቋመው ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። በአረንጓዴ አሻራ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉም የሚታወስ ነው። የችግኝ ተከላው አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን በቀጣይ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ለሚተከሉ ችግኞች እየተካሄደ ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ ኢዜአ የግብርና ሚኒስቴር እና የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ኮሚሽንን አነጋግሯል። የግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ታደሰ በዘንድሮው የክረምት ወቅት የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ህብረተሰቡ ያሳየው ተሳትፎና ፍላጎት መልካም መሆኑን ይገልጻሉ። ለችግኝ ተከላው የተቋቋሙት የብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ እና የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ በአጠቃላይ የተዘረጋው አደረጃጃት ለቀጣይ ስራዎችም ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል። የኃብት፣ የእውቀትና የጊዜ አቅምን በጋራ ለመጠቀም በአገር ደረጃ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት የተደረገው ርብርብ መልካም፣ በርካታ ተቋማት የተሳተፉበትና የአገር በቀል ዕውቀትን መጠቀም ወሳኝ ነው ብለዋል። ሆኖም ከችግኝ ማዘጋጀት አኳያ የነበሩ ክፍተቶች በተከላ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች የችግኝ እጦት እንዲከሰት ማድረጉንና እንደ ዋና ክፍተት መታየቱንም ነው አቶ ተፈራ የገለጹት። ከእጽዋት ዝርያ መረጣና ከችግኝ ተከላ ጋር በተያያዘ መረጃዎችን በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ ከማጠናከር አንጻር ክፍተቶች እንደታዩና ከዚህም ትምህርት በመውሰድ ማስተካከያ ይደረጋል ብለዋል። በክረምት ወቅት የከነበረው ችግኝ ተከላ መነሻ በማድረግ ከወዲሁ ከችግኝ ዝግጅት ጋር በተያያዘ በክልሎች የችግኝ ጣቢያ መለየት ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል። በቅርብ ጊዜም ከክልሎች ጋር በዘንድሮው የችግኝ ተከላ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችና ተግዳሮቶች ምንድናቸው? በቀጣይ ችግሮቹ እንዴት ሊፈቱ ይችላሉ? ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ያሉ አካላት የስራ ድርሻቸው ምን መሆን አለበት በሚለው ዙሪያ ውይይት ተደርጎ እቅድ አጽድቆ ወደ ስራ እንደሚገባም አመልክተዋል። ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴውም አሁን የጀመረውን ስራ በቀጣይ ዓመትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። የግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ታደሰ የሚቀጥለው ዓመት የችግኝ ተከላ በምን አይነት መልኩ እንደሚካሄድም አስረድተዋል። ከሚተከሉ የዛፍ ዝርያዎች አንጻር በችግኝ ተከላው የተለየ ነገር እንደማይኖርና የሚተከሉ የዛፍ ዝርያዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አመልክተዋል። የቀጣይ ዓመት የችግኝ ተከላ ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚጀመርም ጠቁመዋል። አሁን የተጀመረው ስራ ለቀጣይ ሶስትና አራት ዓመታት በዘላቂነት ከተሰራና የእንክብካቤው ስራ በተደራጀ መልኩ ከተከናወነ በደን ልማት ተጨባጭ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ጠቅሰዋል። የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢተው ሽባባው በበኩላቸው በዘንድሮው የችግኝ ተከላ ከቅድመ ዝግጅትና ከበጀት አንጻር ክፍቶች መታየታቸውን ተናግረዋል። ችግኝ ከመትከል አንጻር በባለሙያዎች የአቅም ክፍተት መታየቱንና ይህን ለማስተካከል በቀጣይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል። እንደ ኮሚሽኑ በቀጣይ ዓመት በአንድ ሚሊዮን ሄክታር ላይ 4 ነጥብ 27 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል መታቀዱን ጠቁመዋል። የታቀደውን ያህል ችግኝ ለመትከል ከወዲሁ የችግኝ ተከላ ቦታዎችን መለየትና መረጃ የማደራጀት ስራ እንደሚጀመርም ገልጸዋል። የችግኝ ተከላው ቦታ ከተለየም በኋላ ለችግኝ የሚያስፈልገውን ዘር የማዘጋጀት ተግባር ይከናወናል ብለዋል። ለተከላው የሚያስፈልጉ ጥብቅ ቦታዎችን ከወዲሁ የመለየት ተግባር እንደሚከናወንም ጠቅሰዋል። የችግኝ ተከላው ስራ በዘላቂነት ከተከናወነ ከደን ልማት አኳያ ስለሚገኘው ጥቅም አቶ ቢተው እንደሚከተለው ያስረዳሉ። ችግኝን መትከል ብቻ በራሱ ግብ እንዳልሆና እስኪጸድቁ መንከባከብ የተወሰኑ ተቋማት ስራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም አካላት ድርሻ እንደሆነ በመገንዘብ በችግኝ ተከላው ላይ የሚሳተፉ አካላት በእንክባኬው የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም