ሴቶች በይቻላል መንፈስ ለከፍተኛ አመራርነት ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸው ተመለከተ

73
አዳማ ነሐሴ 09/2011..ሴቶች ከባህልና የአስተሳሰብ ተፅእኖ ተላቀው በይቻላል መንፈስ ለከፍተኛ አመራርነት ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸው በተለያዩ ዩነቨርስቲዎች በምክትል ፕሬዘዳንትነት እያገለገሉ ያሉ ሴት አመራሮች አመለከቱ። በቢሾፍቱ ከተማ እየተሰጠ ባለው በአመራርና ተቋማዊ ለውጥ ስልጠና ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት እነዚህ አመራሮች ለኢዜአ እንዳሉት ሴቶች በመጀመሪያ ለራሳቸው እችላለው የሚል መንፈስ ማዳበር አለባቸው ። የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዘዳንት ወይዘሮ ነፊሳ አልማሃድ በሰጡት አስተያየተ ሴቶች ለቦታው ብቁ ሆነው ከወንዶች እኩል መስራት እየቻሉ ባለባቸው ጾታዊ ተጽዕኖ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው እንደሚያዩ ተናግረዋል። ይህን ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት ከመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ ሴቶችን የማብቃትና የመደገፍ ሥራ መንግስትና ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል። በራስ መተማመን እንዲኖራቸውና ወደ አመራርና ውሳኔ ሰጪነት ቦታ እንዲመጡ የህይወት ክህሎት ስልጠና መስጠት ላይ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባም ጠቁመዋል። በዩኒቨርሲቲዎች ከትምህርት ክፍሎች አመራርነት ጀምሮ በየደረጃው ባሉ የአስተዳደር እርከኖች ላይ እስከ ፕሬዘዳንት ድረስ በልምድና በሥራ ብቃት መምጣት ይኖርባቸዋል። " የተለያዩ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ራሳቸውን ለውድድር ዝግጁ ማድረግ ከኛ ከሴቶች የሚጠበቅ ግንባር ቀደም ተግባር መሆን አለበት" ብለዋል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሴቶች ወደ አመራር እንዲመጡ እየተደረገ ያለው ጥረት ተስፋ ሰጪ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የወሎ ዩኒቨርሰቲ የቢዝነስ ልማትና አለም አቀፍ ግኑኝነት ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር አፀደ ተፈራ ናቸው። "ከታች ያሉትን ሊመሩ የሚችሉ አቅም ያላቸውን ሴቶች ወደ ከፍተኛ የአመራር ቦታ ለማምጣት በልምድና በአቅም ግንባታ በማብቃት ረገድ የአመራርና ተቋማዊ ለውጥ ስልጠና ሚናው የጎላ ነው "ብለዋል። ስልጠናው በየተቋማቱ ያለውን ልምድና ተሞክሮ ለመለዋወጥ እንደሚያግጥ አመልክተው በአመራር አሰጣጥና በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍትሄ ለመስጠት ጭምር የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል። "አሁን ካለንበት ቦታ ወደ ሙሉ ፕሬዘዳንትነት ለመምጣት ለውድድር የሚያበቃን የተሻለ ሥራ መስራት እችለዋለው የሚል መንፈስና በራስ መተማመን አቅም መፍጠር አለብን" ብለዋል። በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ ልማት ዘርፍ ምክትል ፕሬዘዳንት ወይዘሮ ገዳም መንደፍሮ በበኩላቸው የሴት አመራሮችን ብቃት ለማሳደግ ተሳትፎቸውን በማጠናከር ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል። በዚህ ረገድ መንግስት በቅርቡ እየወሰደ ያለው እርምጃ ተስፋ ሰጪና አበረታች መሆኑን ጠቅሰው" ጠንካራ ተሳትፎ፣ድጋፍና ክትትል ሲኖር አቅም ይጎለብታል" ብለዋል። ወይዘሮ ገዳም እንዳሉት ሴቶች ከባህልና የአስተሳሰብ ተፅእኖ ተላቀው በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአመራርነት መስራታቸው ብቻ ሳይሆን በተቋማቱ መማር ማስተማር ላይ ለሚገኙ ሴቶች ምሳሌ ሊያረጋቸው የሚችል ተግባር ማከናወን ይገባቸዋል። የሴቶች ተሳትፎን ለማስፋት በየተቋማቱ ተመርቆ የሚወጡ ሴቶችን ማበረታታት ፣ለውድድር የሚያበቃንን ጥናትና ምርምር በማካሄድ ልምድ ማካበት ከሁላቸውም የሚጠበቅ ቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል። በመንግስት የሚደረግላቸው ድጋፍ ከመጠበቅ አልፈው ያገኙትን አጋጣሚዎች ሁሉ በመጠቀም ተሳትፏቸውን ማስፋትና የእድሉ ባለቤት መሆን እንደሚገባቸው አመልክተዋል። ሴቶች በሳል አመራር ከመስጠት አንፃር ውጤታማ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚንስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማሪያ ናቸው። የሴቶች ተሳትፎና የውሳኔ ሰጪነት ሚና ለማሳደግ መንግስት በክህሎትና አቅም ግንባታ ላይ እየሰራን እንደሚገኝም ገልጸዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም