የሶስተኛ ወገን መድህን ዋስትና የምዝገባ ጊዜተራዘመ

58
ሀዋሳ  ነሐሴ 9/2011 እስከ ነሀሴ 10/2011ዓ.ም ለአንድ ወር ሊካሄድ የነበረው የሶስተኛ ወገን የመድህን ዋስትና ምዝገባ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለሀያ ቀናት መራዘሙን የፌዴራል መድህን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ። በአንድ ወር ውስጥ 168 ሺህ ተሽከርካሪዎች ምዝገባ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል። ኤጀንሲው ከደቡብ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ጋር በመሆን ዛሬ በሀዋሳ በሰጠው መግለጫ በተለይ በደቡብ ክልል በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት የምዝገባ ሂደቱ ላይ መስተጓጎሉን መልክተዋል። በኤጀንሲው የዕቅድና መረጃ ቴክኖሎጂ ዲያሬክተር አቶ መሰረት ገብረኪዳን እንዳሉት በደቡብ ክልል ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለሶስተኛ ወገን የመድህን ዋስትና ምዝገባ ቅድመ ዝግጅት ቢደረግም ምዝገባው በተገቢው ሁኔታ መካሄድ አልተቻለም። በሌሎች ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደሮችም ወጥነት ባለው መልኩ ምዝገባው አለመጠናቀቁን ጠቁመው ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት በመላው ሀገሪቱ የምዝገባው ሂደት እስከ 30/2011 ዓ.ም እንዲራዘም መደረጉን ገልጸዋል። በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ እስካሁን ያልተመዘገቡና ፈቃድ ያላደሱ በህጉ መሰረት ቅጣት እንደሚጣልባቸው የጠቆሙት አቶ መሰረት ለአንድ ወር በተደረገው ምዝገባ በመላ ሀገሪቱ 168 ሺህ ተሽከርካሪዎች የሶስተኛ ወገን የመድህን ዋስትና በመግዛት መመዝገባቸውን አስታውቀዋል። ከተመዝጋቢዎቹም 51 በመቶ የሚሆኑት አዲስ መሆናቸውንና ይህም በሀገሪቱ ካለው የተሽከርካሪ ቁጥር አንጻር አሁንም አነስተኛ ነው ተብሏል። በደቡብ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ኢንፎርሜሽን ብቃት ዳይሬክተር አቶ መርከቡ ታደሰ በበኩላቸው የሶስተኛ ወገን የመድህን ዋስትና ምዝገባ ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም 50 በመቶ ያህል እንኳን እንዳልተመዘገቡ ተናግረዋል። በክልሉ በህዝብ ማመላለሻ መስክ የተሰማሩ ተሽከርካሪዎች የሶስተኛ ወገን መድህን ዋስትና ያልተመዘገቡ ስምሪት ስለማይሰጣቸው አብዛኞቹ መመዝገባቸውን ጠቁመው ይህን ተሞክሮ በሌሎች ተሽከርካሪዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል። ከአስር ሺህ የሚበልጡ ባለሁለት እግር ሞተር ብስክሌቶች በክልሉ ቢኖሩም የሶስተኛ ወገን መድህን የተመዘገቡ ከአንድ መቶ እንደማይበልጡና ሌሎች ተሽከርካሪዎች ጭምር በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ምዝገባ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። በፌዴራል መድህን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሻሬ ኡጋ እንዳሉት ዘንድሮ ሁሉንም ተሽከርካሪዎች ለመመዝገብ ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል። አሁንም የተሰጠውን ጊዜ በመጠቀም ከቅጣት ነጻ የሆነውን ምዝገባ እንዲያከናውኑም ይጠበቅባቸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም