ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ዕድገቷ የአሊባባን ድጋፍ ትፈልጋለች ተባለ

69
ነሐሴ 9/2011 ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፏን ለማሳደግ የአሊባባ ግሩፕን ድጋፍ እንደምትፈልግ  የኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። ይህ የተገለጸው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ከአሊባባ ግሩፕ መስራችና ስራ አስኪያጅ ጃክ ማ ጋር በተቋሙ ዋና መቀመጫ የቻይናዋ  ሃንግዙ ከተማ ተገናኝተው በተነጋገሩበት ወቅት መሆኑን ዢንዋና ቻይና ኦርግ ዶት ኮም ዘግበዋል። ኢንጂነር ጌታሁን “የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚያግዝ ድንቅ ውይይት አድርገናል” በማለት የአሊባባን ዋና መስሪያ ቤት ከጎበኙ በኋላ መናገራቸውም ተገልጿል። የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ጠቀሜታ ለሚሰጠውና በዲጂታል ሽግግር ላይ ላተኮሩ ኢንቨስትመንቶች ቅድሚያ እንደሚሰጥም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች በዘርፉ ፈጣን ለውጥ ለማስመዝገብ የሚረዳ ጉብኝት በአሊባባ ዋና መስሪያ ቤት ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል። የሚኒስትሩ ጉብኝት ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ከጥቂት ወራት በፊት የአሊባባ ግሩፕን ዋና መቀመጫ ከጎበኙ በኋላ የተከናወነ መሆኑ ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጃክ ማ ጋር በስዊዘርላንድ ዳቮስ በጥር 2011 ከተገናኙ በኋላ በድጋሚ በተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ተገናኝተው መወያየታቸው ይታወሳል። በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጃክ ማ ጋር በተገናኙበት ወቅት አሊባባ በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ከተማ የመገንባት ዕቅድ እንዳለው መገለጹ አይረሳም። “ጃክ ማ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ባለው ለውጥ መደነቃቸውንና አገሪቱ ቁልፍ የስትራቴጂክ አጋር መሆኗን መረዳታቸውን " በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት አስታውቆ ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት በአሊባባ ግሩፕ ያለውን ኢንቨስትመንትና ባለሙያዎች ለመሳብ ጥልቅ ፍላጎት እንዳለውና በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለው ጠንካራ የኢኮኖሚ ግንኙነት ለዚህ እንደሚረዳ ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በርካታ የቻይና ኢንቨስትመንት እንደሚገኝና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሃንግዙ የተጓዙት በኢትዮጵያና እንደ አሊባባ ካሉ መሰል የቴክኖለጂ ኩባንያዎች መካከል ትብብር ለመፍጠር፣ ኢንቨስትመንታቸውን በኢትዮጵያ እንዲያፈሱም ለማስቻል መሆኑ ተነግሯል። በተያያዘ በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዳስታወቀው ጃክ ማ በጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ጋባዥነት ህዳር 2012 ዓም ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም