ጃፓን በኢትዮጵያ ለሚካሄደው ብሄራዊ ምርጫ የ3 ሚሊዮን ብር ደጋፈ አደረገች

68
ነሐሴ 9/2011 የጃፓን መንግሥት በኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት ለሚካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ለአቅም ግንባታ የሚውል የ3 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ። የድጋፍ ሥምምነቱን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኬ ማሱናጋና በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይ ቱርሃን ሳሌህ ፈርመውታል። ድጋፉ በመንግሥታቱ ድርጅት የልማት መርኃ ግብር ሥር ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የአቅም ግንባታና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ይውላል ተብሏል። በተለይም የምርጫ ድምፅ መስጫ ሳጥን (ኮሮጆ) እንዲሁም የመራጮችን የጣት አሻራ ለመቀባት የሚያገለግል ቀለም ለመግዛት ይውላል ተብሏል። ጎን ለጎንም ምርጫን መሰረት ያደረጉ አለመግባባቶችን ለመፍታትና ምርጫ ቦርድ መራጮችን ለማስተማር የሚያደርገውን ሥራም ለማጠናከር ያግዛል ነው የተባለው። የምርጫ ድምጽ አሰጣጡ ለመራጮች ግልፅ እንዲሆን ለማስቻል የተደረገው ድጋፍ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ገልጸዋል። ይህም ሕዝቡና ታዛቢዎች በቦርዱ ላይ ያላቸውን አመኔታ እንደሚጨምርላቸው በመጠቆም። በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኬ ማሱናጋና በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥና የተሻሻሉ አሰራሮች እየደገፉና የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይም ደግሞ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዋነኛ አካል የሆነውን ምርጫ መደገፋቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። በመንግሥታቱ ድርጅት የልማት መርኃ ግብር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በማስተባበር በቀጣይ ዓመት የሚካሄደውን የኢትዮጵያ ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ ለማድረግ እየሰራ ነው። ለነዚህም ሥራዎች የሚሆን 40 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተይዞለታል። በቀጣይ ዓመት ከብሔራዊ ምርጫው ጎን ለጎን የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ ምክር ቤቶች ምርጫ እንደሚካሄድ ይጠበቃል። በቅርቡ ገዢው ፓርቲ የኢትዮጵያ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ምርጫው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን መግለፁ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም