የኢትዮ-ሱዳን ጉባኤ የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ትስስር በሚያሳይ አውደ ርዕይ ተጀመረ

62
ባህርዳር ሚያዚያ 26/2010 አራተኛው የኢትዮ-ሱዳን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትብብር ጉባኤ የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ትስስር በሚያሳይ አውደ ርዕይ ዛሬ ተጀመረ። በጉባኤው  ከሱዳን የመጡ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ከባህርዳር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተለያዩ ዝግጅቶችን ለህዝብ እይታ እያቀረቡ ናቸው። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር  ዘውዱ እምሩ  እንደገለጹት ከሱዳን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የምርምር ስራዎችን እያካሄዱ ነው። ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደው የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና የሱዳን ዩኒቨርሲቲዎች የትብብር ስምምነቶች መረሃ - ግብር የኢትዮ ሱዳንን ለዘመናት የዘለቀ ታሪክ በሚዘክር መንገድ መካሄድ መጀመሩን አስታውቀዋል። የሁለቱ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ከአራት ዓመት በፊት በደረሱት ስምምነት መሰረትም አሁን ላይ መምህራንን እየተቀያዩሩ የመማር ማስተማርና የምርምር ስራዎችን በማካሄድ ላይ እንደሚገኙ አውስተዋል። የዘንድሮው የትብብር ጉባኤም ዩኒቨርሲቲዎቹ  እስካሁን በመማርና ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት የተከናወኑ  ስራዎችን በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የሚያስችል ነው። በተለይም የሁለቱ ሀገራት ለዘመናት አብሮ የዘለቀውን የህዝብ ለሀዝብ ግንኙነት የበለጠ ማሳደግ በሚቻለበት ጉዳይ ላይም ይመክራል ተብሏል። የሱዳኑ ኢሚሬትስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ሚስተር ሀሰን አህመድ በበኩላቸው "የትብብር ጉባኤው  የልምድ ልውውጥንና ተሞክሮን በመለዋወጥ ፋይዳው የጎላ ነው "ብለዋል። ከሱዳን የገዳሪፍ ዩኒቨርሲቲና አልዛሪ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ አስር የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ሁለት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች የተውጣጡ ከ80 በላይ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና የሙዚቃ ቡድን ሉዑካን ቡድን ባሀርዳር ገብቷል። ለሶስት ቀናት በሚቆየው የትብብር ጉባኤ የሁለቱን ሀገራት የሚገልጹ የፓናል ውይይት፣ የሙዚቃ ትርኢቶችና የወዳጅነት የእግር ኳስ ጨዎታ እንደሚካሄዱ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም