ልዩነትን ወደ ጎን በመተው በሀገራዊ ጉዳዮች ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

59
ነሐሴ 9/2011 የተለያየ ብሔርና የፖለቲካ አመለካከት ቢኖርም በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ልዩነትን ወደ ጎን በመተው ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ ተነገረ። የኢዜማ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ ለኢዜአ እንደተናገሩት በችግኝ ተከላ የታየው እምርታን ለመድገም በሀገሪቱ የተለያየ ብሔር ና የፖለቲካ አመለካከት ቢኖርም በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ልዩነትን ወደ ጎን  በመተው በአንድነት መስራት ይገባል። በአብሮነት መንፈስ ተባብሮ በመስራት፤ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈንና ልማት ላይ በማተኮር ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ መውሰድ ይቻላልም ነው ያሉት። ለህዝቡ አብሮነትና አንድነት እንቅፋት ለሆኑ የልዩነት ምንጮች መፍትሄ ለመስጠትም የፖለቲከ ፓርቲዎች፣ሲቪክ ማህበራትና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ከህዝብ ጋር መወያየት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት። በጋራ ተባብሮ መስራት ከተቻለ ዜጎቿ ተሳስበው በሰላም የሚኖሩባት ኢትዮጵያን መፍጠር  ይቻላል ያሉት ዶክተር ጫኔ ፤ ለግጭት መነሻ የሆነው ኢ-ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ምላሽ እንዲያገኝ ሥራ አጥነትን በመቅረፍ ና ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ  እንደሚገባም  አብራርተዋል። በህዝቡ መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ትስስር ለማጠናከር ዜጎች ከአንዱ ክልል ወደ ሌላ ክልል ሄዶ እንዲሰሩና በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት የእውቀትና የባህል ልውውጥን እንደሚያጠናክርም ነው የገለጹት። በችግኝ ተከላ የታየውን የህዝቡ ተሳትፎ ና መተባበር በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮችም መድገም እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ናቸው። ከጥቃቅን ርእሰ ጉዳዮች ወጥተን በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፤ ዴሞክራሲ በዳበረባቸው ሀገራት የተለያየ የፖለቲካ ርእዮተ-አለም ያላቸው ሃይሎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ እንደማይደራደሩ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችም እንደመልካም ተሞክሮ ሊወስዱት ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም